በድሬዳዋ ግጭት የተጠረጠሩ 84 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል

255

ድሬዳዋ ጥር 16/2011 በድሬዳዋ የጥምቀትን በዓል ተከትሎ በተከሰተው ግጭት የተጠረጠሩ 84 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።

ኮሚሽኑ አስተማማኝ ሰላም ለማስፈንና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየሰራሁ ነው ብሏል።

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዲቪዥን ኃላፊ ዋና ሳጅን ባንተአለም ግርማ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ጥር 12/2011 ፖሊስ የችግሩ ቀስቃሾች ናቸው ብሎ የጠረጠራቸውን ሰዎች በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያካሄደ ነው፡፡

በተጠርጣሪዎች ላይ መረጃና ማስረጃ አሰባስቦ ለፍርድ ለማቅረብ  የተቀናጀ ሥራ ይከናወናል ብለዋል፡፡

ግጭቱ ከየትኛውም ብሔር ሆነ እምነት ጋር ግንኙነት እንደሌለው ኃላፊው ተናግረዋል።

አንድ መድኃኒት ቤት በከፊል ቃጠሎ እንደደረሰበትም አስታውቀዋል፡፡

በአስተዳደሩ የሕዝቡን ሰላም ለማደፍረስ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ፖሊስና የፀጥታ አካላት ተቀናጅተው እርምጃ እንደሚወስዱ ዋና ሳጂን ባንተዓለም  ገልጸዋል፡፡

ኅብረተሰቡም የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንዲያጎለብት  ጠይቀዋል።

የኢዜአ ሪፖርተር ትናንት ባደረገው ቅኝት ግጭት የተፈጠረባቸው አካባቢዎች ወደ መረጋጋት መመለሳቸውንና ሱቆች በከፊል ተከፍተው ሥራ መጀመራቸውን አረጋግጧል፡፡

በአዲስ ከተማና አካባቢው ወጣቶች ሼል ነዳጅ ማደያ አካባቢ አስተዳደሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎቻቸውን እንዲፈታላቸው ሲጠይቁ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም