''ወጣቱ ኃይል አንድነቱን ጠብቆ በልማትና ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ አለበት''-የኦሮሚያ ክልል ም/ፕሬዚዳንት - ኢዜአ አማርኛ
''ወጣቱ ኃይል አንድነቱን ጠብቆ በልማትና ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ አለበት''-የኦሮሚያ ክልል ም/ፕሬዚዳንት
አዳማ 15/2011 በጅምር ላይ የሚገኘው ለውጥ ለውጤት እንዲበቃ ወጣቱ ኃይል አንድነቱን ጠብቆ በልማትና ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባው የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ጠይባ ሀሰን አስገነዘቡ።
የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ)ወጣቶች ሊግ አራተኛ ጉባዔ ''የወጣቶች አንድነት ለመሰረታዊ ለውጥ!'' በሚል መሪ ቃል በአዳማ ከተማ ዛሬ ተጀምሯል።
በጉባዔው መክፈቻ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ጠይባ ሀሰን እንደገለጹት በጅምር ላይ የሚገኘው ለውጥ ለውጤት እንዲበቃ የወጣቱ ሃይል አንድነትና ጥንካሬ ወሳኝ የሆነበት ምዕራፍ ላይ ይገኛል።
የሊጉ አባላትም ሆነ የክልሉ ወጣቶች አንድነታቸውን ጠብቀው በልማትና ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የሚያደርጉትን ተሳትፎ የትግላቸው ውጤት የሆነው ለውጥ ፍሬ እንዲያፈራ ማድረግ ይገባቸዋል ብለዋል።
የሕዝቡ ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች እንዲመለሱ ወጣቶች በተደራጀ መልኩ ያደረጉት ትግል ዛሬ ለደረስንበት የተስፋ ጭላንጭል የአንበሳውን ድርሻ እንደነበረውም ገልጸዋል።
ወጣቱ ትውልድ የአገሪቷ መፃኢ እድል የሚወስን ኃይል በመሆኑ አሁን በጅምር ላይ ያለውን የለውጥ ምዕራፍ በፍትህ፣በዴሞክራሲና ልማት ታጅቦ ድርብ ድል ለማስመዝገብ ጭምር መሥራት እንደሚጠበቅበትም ምክትል ፕሬዚዳንቷ አስታውቀዋል።
የሕዝቦች አንድነት በተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዋናነት በችግር ወቅት መታጋገዝ ሲኖር መሆኑን አውስተው፣ ለውጡን ለመቀልበስ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጭምር እየተሸረበ ያለውን የፖለቲካ ቁማር በማክሰም አገራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
የኢህዴአግ ወጣቶች ሊግ ሊቀመንበር ወጣት ሙቀት ታረቀኝ በበኩሉ በከፍተኛ አስተዋይነትና ጥንቃቄ የወጣቶችን የትግል ስልት ተቋማዊ በማድረግ ዛሬ የአገሪቷ ህዝቦች የዴሞክራሲ ተስፋ እንዲለመልም መሪ ድርጅቱ፣ ኦዴፓና አባላቱ የተጫወቱት ሚና የማይተካ ነበር ብሏል።
''የሕዝብ አንድነት ኃይል፣ነፃነትና ዴሞክራሲ ነው'' ያለው ለቀመንበሩ፣የለውጥ ጉዞው ስኬታማ እንዲሆን ወጣቱ በማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባው ገልጿል።
የመንጋ ፍትህ በማስቀረት፣በክልሉም ሆነ በአገር ደረጃ የሕግ የበላይነት እውን እንዲሆንና አስተማማኝ ሰላም በማረጋገጥ ላይ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቋል።
ለዚህም ወጣቱ ኃይል የፖለቲካ ቁማርተኞች አፍራሽ ዓላማ ማስፈፀሚያ መሣሪያ ሳይሆን፤ በትምህርትና በልማት፣ራሱንና አገሩን መለወጥ በሚችልበት ሂደት ላይ ሙሉ ትኩረት በማድረግ የለውጡ ቁልፍ አጋዥ መሆን እንደሚገባው አመልክቷል።
የህዝቡና የወጣቶች የተቀናጀ ትግል ክልሉም ሆነ አገሪቷ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ መክፈቱን የገለጸው ደግሞ የኦዴፓ ወጣቶች ሊግ ሊቀመንበር ወጣት ሀሰን ዑሳ ነው።
ባለፉት ሶስት ዓመታት በመንግሥታዊ የአስተዳደር መዋቅሮች የተንሰራፋው ብልሹ አሰራር፣ሙስናና የተደራጀ ሌብነትና ዝርፊያ የወጣቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጥያቄ እንዳይመለስ ማድረጉን ገልጿል።
በወጣቶች መስዋዕትነት የተገኘውን ድልና የለውጥ ጉዞ በውጤት በማጀብ ከግብ ማድረስ አለብን ብሏል።
ለሶስት ቀናት በሚቆየው ጉባዔ አገራዊ ለውጡን በተቀናጀ መልኩ በሚያስቀጥሉ አጀንዳዎች ላይ ጥልቅ ውይይት ይደረጋል።
የሊጉ ሥራ አስፈፃሚዎችና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እንደሚመረጥ ከመርሐ ግብሩ ለማወቅ ተችሏል።