ቡናን በህገ-ወጥ መንገድ ያጓጓዘው ግለሰብ በእስራትና በገንዘብ ተቀጣ

50

አምቦ ጥር 15/2011 በህገ-ወጥ መንገድ ቡና ሲያጓጉዝ ተገኝቷል ተብሎ የተከሰሰው ግለሰብ በሁለት ዓመት እስራትና በገንዘብ  እንዲቀጣ መወሰኑን በደቡብ ምዕራብ ዞን  የወሊሶ ወረዳ ፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡

ውሳኔው የተላለፈው አብርሃም ከፍያለው  በተባለ አሽከርካሪ ላይ ነው፡፡ 

የወረዳው ፍርድ  ቤት ፕሬዘዳንት አቶ ወጋሪ ፉፋ ለኢዜአ እንደገለጹት ግለሰቡ ጥር 13/ 2011ዓ.ም. ሌሊቱ ስምንት  ሰዓት አካባቢ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-58774 አ.አ. በሆነ አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ በርበሬ ከላይ ከስር ደግሞ  በህገ-ወጥ መንገድ 40 ኩንታል ቡና ጭኖ ተገኝቷል።

" ግለሰቡ ከጅማ  ወደ አዲስ አበባ ቡናውን በማጓጓዝ ላይ እንዳለ ወሊሶ ከተማ ላይ ተይዟል"ብለዋል ።

ጉዳዩን የተመለከተው  የወሊሶ ወረዳ ፍርድ ቤት ዛሬ በዋለው  ችሎት ከእስራቱ በተጨማሪ በ10 ሺህ ብር እንዲቀጣ ውሳኔ ማስተላለፉን ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል ።

በኤግዝቢትነት የተያዘው 20 ኩንታል በርበሬና 40 ኩንታል ቡና ለመንግስት ውርስ እንዲሆን መወሰኑንም አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም