ቀጥታ፡

የ2011 የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ የፊታችን ዓርብ ይጀምራል

አዲስ አበባ ጥር 15/2011 የ2011 የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ የወንዶች ፕሪሚያር ሊግ የፊታችን ዓርብ በክልል በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጀምራል።

የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይመር ኃይሌ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት የዘንድሮው ውድድር በአዲስ ፎርማት እንደሚደረጉ ነው።

የውድድር ፎርማቱ በአዲስ መልክ እንዲደረግ ያስፈለገው ክለቦች በቂ የውድድር እድል በአነስተኛ የገንዘብ ወጪ ለማድረግ ታስቦ እንደሆነም ነው የተናገሩት።

ስድስት ክለቦች በሁለት ምድብ ተከፍለው የሚጫወቱበት ይህ ውድድር የፊታችን ዓርብ የሚጀምር ይሆናል።

በዚህ መሰረትም ወልቂጤ ከተማ፣ ጎንደር ከተማና የካ ክፍለ ክፍለ ከተማ በአንድ ምድብ ሀዋሳ ከተማ ፣ኢትዮጵያ ውሃ ስፖርትና አዳማ ከተማ  ደግሞ በሁለተኛ ምድብ የተደለደሉ ክለቦች ናቸው።

ውድድሩ ከነገ በስቲያ ሲጀመር በምድብ አንድ ላይ የተደለደሉት ሶስቱ ክለቦች ወደ ወልቂጤ በማቅናት ለሶስት ተከታታይ ቀናት እርስ በእርሳቸው የሚጫወቱ ይሆናል።

በተመሳሳይ በምድብ ሁለት የተደለደሉት ክለቦች ሀዋሳ ላይ ለሶስት ተከታታይ ቀናት እርስ በእርሳቸው የሚጫወቱ ይሆናል።

ከ15 ቀናት በኋላ ደግሞ በምድብ አንድ ላይ የሚገኙት የካና ወልቂጤ ከተማ  ወደ ጎንደር በማቅናት እርስ በእርሳቸው ሶስቱ ክለቦች የሚገናኙ ይሆናል።

በተመሳሳይ ጎንደር ከተማና ወልቂጤ ከተማ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት አዲስ አበባ ላይ ከየካ ክፍለ ከተማ ጋር እርስ በእርስ የሚጫወቱ ይሆናል።

በምድብ ሁለት የተደለደሉ ክለቦችም ከምድብ አንድ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ በሚገኙበት ከተማ በዙር ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል።

በዚህ መልኩ በሁለቱ ምድቦች የሚገኙት ክለቦች በሜዳቸው ጨዋታቸውን ካደረጉ በኋላ ከሁለቱ ምድብ አንደኛና ሁለተኛ የሚወጡ ክለቦች በአንድ ምድብ ተደልድለው ለደረጃ እርስ በእርስ ክለቦቹ በሚገኙበት ከተማ በመሄድ የሚጫወቱ ይሆናል።

ከሁለቱ ምድብ ሶስተኛ የወጡት ክለቦች ደግሞ  በሜዳቸውና ከሜዳቸው ውጭ ጨዋታቸውን የሚያደረጉ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ከሚያደጋቸው የክልል ሻምፒዮና የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች በተጨማሪ ፕሪሚያር ሊግ ደረጃ ውድድሮቹን ሲያካሄድ ዘንድሮ ለስድስተኛ ጊዜ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም