በድሬዳዋ ከተማ የተከሰተው የወጣቶች ግጭት የዕምነት መሰረት የለውም...የኃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ ከተማ የተከሰተው የወጣቶች ግጭት የዕምነት መሰረት የለውም...የኃይማኖት አባቶች
ድሬዳዋ ጥር 14/2011 በድሬዳዋ ከተማ ላለፉት ሁለት ቀናት የተከሰተው የወጣቶች ጸብ ከኃይማኖት ጉዳይ ጋር የማይገናኝ መሆኑን የከተማዋ የኃይማኖት አባቶች ተናገሩ፤
ግጭቱን የፈጠሩ አካላትም ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
የክርስትናና የእስልምና ኃይማኖት አባቶች ወቅታዊ ጉዳይን አስመልክቶ ማምሻውን በሰጡት መግለጫ የሁለቱ እምነት ተከታዮች ለበዓሉ ድምቀትና ማማር ተቀናጅተው የሚያኮራ ሥራ መስራታቸውን ገልፀዋል፡፡
የድሬዳዋ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ ሊቀ-ብርሃናት ቀለመወርቅ ቢምረው ግጭቱን የፈጠሩት ድብቅ ፍላጎት ያላቸው አካላት እንጂ ከኃይማኖት ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው አስረድተዋል።
"ታቦቱ ከገባ በኋላ ታቦቱን ያጀበው ሰረገላና ወጣቶች ላይ ከድብቅ ስፍራ ድንጋይ ተወረወረ፤ ወጣቱ ድንጋይ ወደ ተወረወረበት በመሄድ ጸቡ ተፈጠረ" ብለዋል።
ያጠፋና አካል በሰማያዊም ሆኑ በምድራዊው ህግ እንደሚዳኝ ገልጸው በተከሰተው ግጭት በቤተክርስቲያናት ላይ ምንም አይነት ጥፋት አለመድረሱን አረጋግጠዋል፡፡
የድሬዳዋ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ኃላፊ ሼህ ኢብራሂም ኢማም አህመድ በበኩላቸው በከተማው የኃይማኖት ተቋማት ለሰላም መስፈን፤ ለኃይማኖታዊ በዓላት መድመቅና ማማር በጋራ የሚሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ባለፉት ሶስት ቀናትም ተመሳሳይ ሥራ መስራቱን ተናግረው በዓሉ በደመቀ መንገድ በተጠናቀቀበት መጨረሻ ሰዓት የተፈጠረው ችግር የተደበቀ ዓላማ ያነገቡ አካላት የፈጠሩት ሴራ ያስከተለው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ድርጊቱን አውግዘው ፣ የተፈጠረው ግጭት ከኃይማኖት ጋር የሚያገናኘው አንዳችም ነገር አለመኖሩን ሼህ ኢብራሂም ገልፀዋል፡፡
"በዚህ ጥፋት የተሳተፉ ሰዎች ታድነው ለህግ መቅረብ አለባቸው፤ በግርግር ውስጥ ዘረፋ የፈፀሙ ሰዎችም ተገቢውን ቅጣት ማግኘት ይገባቸዋል"ብለዋል፡፡
"ከሁሉም በላይ ወጣቶች መቼም ቢሆን ባልተረጋገጠ አሉባልታ ከመመራት እራሳቸውን መጠበቅ አለባቸው" ብለዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ እስቅያስ ታፈሰ ወቅታዊ ጉዳይን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት ባለፉት ሶስት ቀናት የከተራና የጥምቀት በዓል ፍፁም ሰላማዊና አስተማማኝ እንዲሆን የሁለቱ እምነት ተከታዮች ተቀናጅተው ሰርተዋል፡፡
"ትላንት ማምሻውን የእግዚአብሔር አብ ታቦት ወደ ማደሪያ ከገባ በኋላ ታቦቱን ባጀበው ሰረገላና ሰረገላውን ባጀቡት ወጣቶች ላይ ድንጋይ ተወርውሮ ችግሩ መቀስቀሱን ፖሊስ አረጋግጧል" ብለዋል፡፡
የተፈጠረው ትንኮሳ በአብዛኛው የኃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ ቁጣ መፍጠሩንና አስከ ቀኑ ስምንት ሰዓት ድረስ ወጣቶች በድንጋይ ሲጣሉ እንደነበር ገልፀዋል፡፡
በአሁን ሰዓት የፀጥታው ኃይል ችግሩን ተቆጣጥሮ የማረጋጋት ሥራ እየሰራ መሆኑን ገልጸው "በግጭቱ የሰው ህይወት አላለፈም፤ ከፍተኛ ጉዳት አልደረሰም፤ የተጎዳ አንድም ቤተክርስቲያን የለም"ብለዋል፡
ግጭቱ እንዲቀሰቀስ ያደረጉና ጥፋት ያደረሱ አካላትን በቁጥጥር ሥር ለማድረግ በፖሊስ የተቀናጀ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
መሰል ጥፋት ባነገቡ አካላት ላይ ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ በሚደርገው ጥረት ህብረተሰቡ የድርሻቸውን መወጣት እንዳለበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የሲቲ ዞን የበርበርታ ወጣቶች ማህበር ሊቀመንበር ወጣት ጣሂር ፋራህ ሰመሬ በበኩሉ በበዓሉ ላይ የተፈጠረው ድርጊት የሚወገዝና የድሬዳዋ መገለጫ አለመሆኑን ተናግሯል።