ቀጥታ፡

ለፕሮጀክቶች በወቅቱ መጠናቀቅ ሙያዊ ስነ-ምግባርን መላበስ ይገባል-ኢንጅነር አፈወርቅ በዛብህ

አዲስአበባ ትር 14/2011 ለፕሮጀክቶች በወቅቱ መጠናቀቅ ሙያዊ ስነ-ምግባርን መላበስ እንደሚገባ በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የኢንጅነሪንግና ማኔጅመንት ስልጠና ዳይሬክተር ኢንጅነር አፈወርቅ በዛብህ ተናገሩ።

በአሜሪካን አገር ነዋሪ በሆኑት ኢንጅነር በላይ ኪዳኔ የሚተዳደረው የበጎ አድራጎት ድርጅት በፕሮፌሽናል ምህንድስና ስነ-ምግባር ላይ ስልጠና ሰጥቷል።

በስልጠናው የአገር ውስጥና የውጭ ተቋራጮች፣ አማካሪዎች፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የኮንስትራክሽን አስተዳደርና ፕሮጀክት ፕሮግራም ጋር ተያያዥ ስራዎች የሚሰሩ መሃንዲሶች እንዲሁም የመስሪያ ቤቱ የስነ-ምግባር ዳይሬክተሮች ተካተዋል።

የባለስልጣኑ የኢንጅነሪንግና ማኔጅመንት ስልጠና ዳይሬክተር ኢንጅነር አፈወርቅ በዛብህ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ለፕሮጀክቶች በወቅቱ መጠናቀቅና በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ማስረከብ ሙያዊ ስነ-ምግባርን በተላበሰ መንገድ መስራትን ስለሚጠይቅ ለዚህም የጋራ መግባባት ለማምጣት የሚቻልበትን መንገድ ለመዘርጋት የሚረዳ ስልጠና ነው።

ተቋሙ የራሱ የሆነ የስነ-ምግባር መርሆዎች አሉት ያሉት ኢንጅነሩ፤ ነገር ግን "ምን ያህል ተግባራዊ እያደረግሁ ነው?" የሚለውን ፈትሾና በቀጣይም እያንዳንዱ ባለሙያ ሙያዊ ስነ-ምግባሮችን አክብሮ ለመስራት መፈራረምን የሚጠይቅ ነው ብለዋል።

ኢንጅነር በላይ ኪዳኔ በበኩላቸው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያን  ምሁራንና እያንዳንዱ ባለሙያ ሙያዊ ስነ-ምግባሩን በመወጣት የተጀመረውን ለውጥ ማስቀጠል አለበት።

አላማውም የመጣውን ለውጥ ለማበረታታትና ያደጉ አገሮችን ተሞክሮ በማምጣትና አሰራሩን በማሳለጥ በሙያችን የሚጠበቅብንን አሻራ ለማሳረፍ ነው ብለዋል።

ሰልጣኞች በበኩላቸው በሙያው የሚታዩ ክፍተቶችን ሙያው የሚጠቀውን ስነምግባር ያልተወጡ ባለሙያዎች ላይ እርምጃ ከመውሰድ በፊት ስነ-ምግባሮችን እንዴት የጋራ አድርገን ሙያችንን አንድ እርምጃ ማሳደግ አለብን የሚለውን እንድንረዳ አድርጎናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም