ለድሬዳዋ ችግር ዘላቂ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

60

ድሬደዋ ጥር 14/2011 በድሬዳዋ ከተማ እየተፈጠረ ላለው የጸጥታ ችግር ዘላቂ መፍትሄ እንደሚያስፈግ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ወጣቶች ገለጹ፡፡

በድሬዳዋ ትላንትና ዛሬ ለተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ ዋና መንስኤ ስልጣናቸውን የተነጠቀባቸው አካላት የፈጠሩት ሴራ በመሆኑ አጥፊዎችን በማጋለጥ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

በድሬዳዋ የከተራና የጥምቀት በዓል በደመቀ ሥነ-ሥርዓት እንዲከበር የእስልምናና የክርስትና እምነት ተከታዮች ከፍትህ አካላት ጋር ተቀናጅተው መሰራታቸውን ወጣቶቹ ተናግረዋል፡፡

ወጣቶቹ እንዳሉት በዓሉ በደምቀት የተከበሩ ቢሆንም የመጨረሻው የእግዚአብሔር አብ ታቦት ትላንት ማምሻውን ወደ ማደሪያው በገባበት ወቅት ሁከትና ብጥብጥ ተፈጥሮአል፡፡

ወጣት ዮሐንስ አበበ በወቅቱ በሥፍራው እንደነበር አስታውሶ  ታቦት ከገባ በኋላ  በወጣቶች መካከል  በተፈጠረው ጥል ለረብሻው ምክንያት መሆኑን ገልጿል፡፡

ወጣት ፍቅሩ ፋንታሁን በበኩሉ ወጣቱ ከሁሉም ማዕዘን በመሰባሰብ  ጥፋት እንዳይፈፀም  በተሰማራበት ወቅት በወጣቶች መካከል ችግር በመፍጠሩ የፀጥታ አካላት ገብተው  ጥሉን ማብረዳቸውን ጠቁመዋል፡፡

ወጣት አብዱልፈታህ መሐመድ በሰጠው አስተያየት ደግሞ  ለችግሩ ዋና መንስኤ የባለሥልጣን ስውር እጅ እንዳለበት ተናግሯል፡፡ 

" ከስልጣን የተወገዱ አካላት የጠነሰሱት ድብቅ ሴራ ውጤት ነው " ብሏል፡፡

ወጣቶች እንደተናገሩት ለድሬዳዋ ችግር ዘላቂው መፍትሄና ለህግ የበላይነት መረጋገጥ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ መስራት አለበት፡፡

ግጭቱን ተከትሎ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በድል ጮራና በድሬዳዋ ጤና ጣቢያ ህክምና  ተሰቷቸው ወደ ቤታቸው መመለሳቸው በስፍራው የሚገኘው የኢዜአ ሪፖርተር አረጋግጧል፡፡

በታክሲዎች፣ በሆቴልና በእቃ መጋዘኖች ላይ ጉዳት መድረሱን ፣ በአሁኑ ወቅት አካባቢው መረጋጋቱንና  አጥፊዎችን ለመያዝ ፖሊስና ህብረተሰቡ ተቀናጅተው እየሰሩ መሆናቸውን ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም