ለሀገር ሰላም መከበር ወጣቱ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ---አቶ ሞገስ ባልቻ - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገር ሰላም መከበር ወጣቱ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ---አቶ ሞገስ ባልቻ
ሀዋሳ ጥር 14/2011 በሀገሪቱ ያለውን ለውጥ ለማደናቀፍ የሚጥሩ ኃይሎችን በማጋለጥ ለሰላም መከበር ወጣቱ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ አሳሰቡ።
የደኢህዴን ወጣቶች ሊግ አራተኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተጀምሯል።
በጉባኤው መክፈቻ ስነሰርዓት አቶ ሞገስ እንዳሉት ደኢህዴን የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ያልተደፈሩ ጉዳዮችን በመድፈርና እርምጃ በመውሰድ ለረጅም ዘመናት ሲንከባለሉ የነበሩ የህዝብ ጥያቄዎችን በብቃት በመመለስ ላይ ይገኛል።
ባለፉት አስር ዓመታት የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደ መሪ ድርጅት የተሰሩት የወጣቶች ውሳኔ ሰጪነት ለማጎልበት የሚያስችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
"የክልሉ ወጣቶች የተለያየ ይዘት ያላቸው የፖለቲካ ጥያቄዎች እንዳሏቸው የክልሉ መንግስት ያምናል" ያሉት አቶ ሞገስ በሀገሪቱ የተቀጣጠለው ለውጥ ለጥያቄዎቻቸው ተገቢውን መልስ እንደሚሰጥም ጠቁመዋል።
ለዚህም ሀገራዊ ለውጡ ያለምንም የጸጥታ ችግርና ሁከት ህዝባዊ ትስስሩ ሳይጎዳ በሙላት እንዲተገበርና በወጣቶች ተሳትፎ እውን እንዲሆን ማድረግ ተገቢ እንደሆነ ገልጸዋል።
ወጣቱ ከማንኛውም ሰላምን ከሚጎዳ ድርጊት ራሱን እንዲያርቅና ሌሎችም እንዲርቁ በማድረግ ሀገራዊ ለውጡ በሙላት እንዲተገብር ኃላፊነቱ ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የደኢህዴን ወጣቶች ሊግ ፕሬዝዳንት ወጣት አክሊሉ ታደሰ በበኩሉ ሊጉ ከምስረታው ጀምሮ የተደራጀበትን ዓላማ ለማሳካት የተለያዩ ስልቶችንና ስትራተጂዎችን በመንደፍ ሲሰራ መቆየቱን ተናግሯል።
ምክንያታዊ ወጣት ለማፍራት በሚያስችል መልኩ የተለያዩ የክርክርና የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ችግሮቹን ለይቶ በስራ እድል ፈጠራ መስክ ብዙዎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ አመልክቷል፡፡
የወጣት ሊጉ አባላት ያለባቸውን የስራ አጥነት ችግር ለመፍታት በተከናወነው ተግባር ከ387 ሺህ በላይ ወጣቶችን በገጠርና በከተማ በተለያዩ መስኮች እንደሰማሩ መደረጉን ፕሬዝዳንቱ ጠቁሟል።
በፖለቲካው መስክ በተለያዩ አደረጃጀቶች የወጣቱን ተሳትፎ ለማሳደግ የተከናወነው ስራም አጥጋቢ ውጤት እንደተመዘገበበት አሰረድቷል።
ለዚህ ቀጣይነት ወጣቱ ከምንግዜውም በተለየ መልኩ በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ለማሳካት የሰላም አምባሳደር መሆን እንዳለበት ጠቁሟል።
የደኢህዴን ወጣቶች ሊግ የወጣቶች የስራ እጥነት ችግር በመቀነስ በክልሉ የተረጋጋ ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ በኩል የተከናወኑ ስራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን የተናገረው ደግሞ የኢትዮጵያ ወጣቶች ሊግ ፕሬዝዳንት ወጣት ሙቀት ታረቀኝ ነው፡፡
በክልሉ ወጣቱን በማህበራዊ ፣ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ተጠቃሚ ለማድረግ የተከናወኑ ስራዎች ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለባቸውም ጠቁሟል፡፡
የደኢህዴን ወጣቶች ሊግ አራተኛ መደበኛ ጉባኤ" ምክንያታዊ ወጣት ለሀገራዊ ለውጥ" በሚል መሪ ሀሳብ ለሶስት ቀናት እንደሚቆይ ታውቋል፡፡