ከ13 ሺህ በላይ ሰዎች የምህረት አዋጁ ተጠቃሚ ሆኑ

117

ጥር 14/2011 ካለፈው ሃምሌ ወር ጀምሮ ላለፉት ስድስት ወራት ተግባር ላይ  በዋለው የምህረት አዋጅ መሰረት ከ13 ሺህ በላይ ሰዎች ወንጀላቸው ሙሉ  ለሙሉ እንደተሰረዘላቸው የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ።

የምህረት ሰርተፊኬት የወሰዱት ሰዎች ቁጥር ከዚህም በላይ እንደሚጨምር ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የገለጸ ሲሆን የሶስት ክልሎችና የመከላከያ ሠራዊት የተወሰኑ ክላስተር መረጃዎች እንዳልተላኩለት ጠቁሟል።

የተቋሙየህዝብ ግንኙነትዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ ለኢዜአ እንደተናገሩት አዋጁ ስራ ላይ ከዋለበት ቀን ሃምሌ 13/2010 ዓ.ም እስከ ተጠናቀቀበት ጥር 13 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ በርካታ ግለሰቦች ተጠቃሚ ሆነዋል።

በፌደራል ደረጃ ተፈርዶባቸው በማረሚያ ቤት የነበሩ 250 ግለሰቦች ምህረት ተደርጎላቸው መፈታታቸውን ገልጸዋል።

ተጠርጥረው የሚፈለጉ፣ ክስ ላይ ያሉ፣ በሌሉበት የተፈረደባቸው በጥቅሉ 430 ሰዎች የምህረት ሰርተፍኬት የወሰዱ ሲሆን፥ ምህረት በሚያሰጥና በማያሰጥ ወንጀል የተፈረደባቸው 162 ሰዎች ሰርተፍኬት መውሰዳቸውን ነው የጠቀሱት።

በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ሆነው በኦንላይን በማመልከት 160 ሰዎች የምህረት አዋጁ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በክልል ደረጃ ምህረት የተደረገላቸው ሰዎች መረጃ የማጠናቀር ስራ እየተጠናቀቀ መሆኑን ገልጸዋል።

ኦሮሚያ ክልል 62፣ አማራ 2 ሺህ 923፣ ትግራይ 144፣ ደቡብ ክልል 108፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል 94፣ ሀረሪ ክልል 50 ሰዎች እስከ ትናንት ድረስ የምህረት አዋጁ ተጠቃሚ ሆነዋል።

አቶ ዝናቡ የጋምቤላ፣ አፋርና ሶማሌ ክልሎች መረጃ አልተጠናቀረም ነው ያሉት።

ምህረት የተደረገላቸው የፌደራል ፖሊስና የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላትን በተመለከተም አቶ ዝናቡ መረጃ ሰጥተውናል።

በዚህም መሰረት በምህረት አዋጁ 2 ሺህ 131 የፌደራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም ከመከላከያ ሰራዊት የቤላ ክላስተር ብቻ ለ6 ሺህ 655 ሰዎች ምህረት ተደርጎላቸዋል ነው ያሉት።

የመከላከያ ሰራዊት የሌሎች ክላስተሮች መረጃ ለፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ገና እንዳልተላከለትም አቶ ዝናቡ ጠቁመዋል።

ጥር 13 ቀን 2011 ዓ.ም ቀነ ገደቡ የተጠናቀቀውአዋጁ ከግንቦት 30 ቀን 2010 ዓ.ም በፊት ለተፈጸሙ ወንጀሎች ይመለከታቸዋል ለተባሉግለሰቦች ምህረት ለማድረግ ስራ ላይ መዋሉን ነው የጠቀሱት።

አዋጁ ተፈጻሚ የሆነው ምህረት ለመስጠት በውስጡ ባካተታቸው ወንጀሎች ውሳኔ ለተላለፈባቸው፣ ተጠርጥረው ለተያዙና ክስ ለተጀመረባቸውብቻ ነው ብለዋል።

አቶ ዝናቡ የምህረት አዋጁ የተጀመረውን ለውጥ የበለጠ ለማሳለጥ፣ ከወንጀሉ ነጻ ሆነው በጥሩ ዜጋነት ሀገራቸውንና ህዝባቸውን እንዲያገለግሉራሳቸውም የዴሞክራሲ መብቶቻቸውን እንዲተገብሩ ፋይዳው የላቀ መሆኑን አንስተዋል።

አዋጁ የተቀጠመለት ቀነ ገደብ ትናንት የተጠናቀቀ ሲሆን የምህረት ተጠቃሚ ለመሆን የሚያመለክቱ ሰዎች ቁጥር ከጨመረ ለመንግሥት መረጃው ቀርቦ ውሳኔ እንደሚሰጥበት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም