የአለም ኢኮኖሚ ፎረም አመታዊ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ ይጀመራል

138

አዲስ አበባ ጥር 14/2011 የአለም ኢኮኖሚ ፎረም ዓመታዊ ጉባኤ ዛሬ በስዊዘርላንድ ዳቮስ ይጀመራል ተብሎ እየተጠበቀ ነው።

ለመጪዎቹ ሶስት ቀናት በሚቆየው ጉባኤ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድን ጨምሮ 60 የሚሆኑ መራሄ መንግስታትና 2 ሺህ የሚጠጉ የንግድ ተቋማት ኃላፊዎች ይሳተፋሉ።

ከመላው አለም የተሰባሰቡ 3 ሺህ የሚጠጉ የአገራት መሪዎች፣  የሲቪል ማህበረሰብ መሪዎች፣ ምሁራንና የሚዲያ አካላት ይሳተፋሉ።

ጉባኤው በአራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን አለም አቀፍ ንድፍ እናስቀምጥ በሚል እሳቤ ነው የሚካሄደው።

ጉባኤው ለሰላም፣ ለአሳታፊነት እና አለም ወደፊት የምትፈጥረውን ትብብር ቀጣይ ማድረግ ላይ ሞዴል በማስቀመጥ ላይ ያተኩራል።

አሁን ያለው የአለም አገራት አስተዳደር አገራት ያላቸውን ልእለ ኃያልነት ለማስጠበቅ የሚሻኮቱበትና ትኩረት ያደረጉበት መሆኑም ተጠቅሷል።

 የፎረሙ መስራችና ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ክላውስ ሽዋብ “አራተኛው የሉላዊነት ሰደድ ሰዎችን ማዕከል ያደረገ፣አሳታፊና ቀጣይነት ያለው መሆን አለበት" ብለዋል።

"የጉባኤው ተሳታፊዎችና ባለድርሻ አካላት ይህን ችግር በመጋፈጥ ጋሬጣውን ለማስወገድ ቁርጠኛ መሆን አለባቸው” ሲሉም ተናግረዋል።

የዘንድሮው ጉባኤ 350 መድረኮችን የሚያስተናግድ ሲሆን የሚቀርቡት ጥናቶችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ዘላቂ መፍትሄ ያስገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም