ፍርድ ቤቱ በከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት በተጠረጠሩት 5 ሰዎች ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ

አዲስ አበባ ጥር 13/2011 የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት በከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር በዋሉት 5 ሰዎች ላይ የተጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ።

ተጠርጣሪዎቹ በነ ጎህ አጽባሃ መዝገብ በከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀል በቁጥጥር ስር ከዋሉት 33 ሰዎች መካከል ናቸው።

እነዚሁ ተጠርጣሪዎች ቁጥራቸው በርካታ በመሆኑ የተፋጠነ የፍትሕ ስርአት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ሲባል አራት ቦታ ተከፍለው ጉዳያቸው በተለያዩ ቀናት ለየብቻ እንዲታይ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መወሰኑ ይታወቃል።

በዛሬው ዕለትም በዚሁ መዝገብ ውስጥ ተጠርጣሪ ከሆኑት ውስጥ ኮማንደር አለማየሁ ኃይሉ፣ ምክትል ኢንስፔክተር የሱፍ ሐሰን፣ ኢንስፔክተር ምንላርግልህ ጥላሁን፣ ዋና ሳጁን ርዕሶም ክህሽንና ኢንስፔክተር ፈይሳ ደሜ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

መርማሪ ፖሊስን ተክቶ ፍርድ ቤት የቆመው አቃቤ ሕግ ለ10ኛ ወንጀል ችሎት እንዳቀረበው በሁሉም ተጠርጣሪዎች ላይ ቅድመ ምርመራ ለማድረግ ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጠኝ ይገባል ሲል ጠይቋል።

አቃቤ ህግ ከዚህ በተጨማሪ ምስክሮች ደህንነታቸው የተጠበቀና የተመቸ ቦታ ሆነው ቃላቸውን እንዲሰጡ ለማድረግና የሕክምና ማስረጃዎችን የማሰባሰብ ስራን ለማከናወን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ያስፈልገኛል ነው ያለው።

ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው ፖሊስ በየወቅቱ ለተጨማሪ የጊዜ መጠየቂያ የሚያቀርባቸው ስራዎቹ ተመሳሳይነት ያላቸው ናቸው ፤የዋስትና መብታችን ሊከበር ይገባል ተጨማሪ ጊዜው ሊሰጥ አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል።

የግራ ቀኝ ክርክሩን የሰማው ፍርድ ቤቱ አቃቤ ሕግ ከጠየቀው ከ14 ቀን ውስጥ 9ኙን ቀን ፈቅዶ ለጥር 21 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም