ዩኒየኑ የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ አልተወጣም ሲሉ አባላት ቅሬታቸውን ገለጹ

36

 ደሴ  ጥር 12/2011  የእሪኩም ሁለገብ  የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበር ዩኒየን ገበያውን በማረጋጋትና አባላትን ተጠቃሚ  በማድረግ በኩል  የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ እንዳልተወጣ  በመግለጽ የዩኒየኑ አባላት ቅሬታቸውን አሰሙ፡፡

ዩኒየኑ 13ኛውን መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በደሴ ከተማ አካሂዷል፡፡

ከዩኒየኑ አባላት መካከል በኩታ በር ወረዳ የሚገኘው የቆንዲ መሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበር አንዱ ነው፡፡

የማህበሩ አባል የሆኑት በወረዳው የቀበሌ 013  አርሶ አደር አሊ ይመር ትናንት በተካሄደው የዩኒየኑ ጉባኤው ወቅት እንዳሉት  ዩኒየኑ ገበያውን የሚያረጋጋና አባላቱን ተጠቃሚ የሚያደርግ የተሳካ ግብይት እያከናወነ አይደለም።

" በማህበራችን በኩል የዩኒየኑ አባል ስንሆን ያመረትነውን ምርት በተሻለ ዋጋ ሊገዛንና መሰረታዊ ሸቀጣሸቀጦችንም  በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረብ ዓላማ እንዳለው ተነግሮን ነበር " ብለዋል፡፡

ሆኖም ይህንን ኃላፊነቱን በአግባቡ ባለመወጣቱ  በተለመደው አካሄድ በአካባቢያቸው  ግብይት ለመፈጸም በመገደድ ለኪሳራ መጋለጣቸውን በመግለጽ ቅሬታቸውን በጉባኤው ሂደት አሰምተዋል፡፡

ሌላው ቅሬታቸውን ያሰሙት በኮምቦልቻ ወረዳ  የሰኞ ጦቢላ መሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበር አባልና የቀበሌ ስድስት አርሶ አደር ሰይድ አሊ ናቸው፡፡

ቀደም ሲል ያመረቱትን ማሽላ በተሻለ ዋጋ ለማህበራቸው በመሸጥ በቆሎ፣ ጤፍና ሸቀጣሸቀጥ እንዲሁም የፋብሪካ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ይቀርብላቸው እንደነበረ አርሶ አደሩ አስታውሰዋል፡፡

ማህበራቸው የዩኒየኑ አባል ሆኖ ሲደራጅ የተሻለ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ቢሆንም  አሁን ላይ ግን በዩኒየኑ በኩል የሚቀርብላቸው የፍጆታ ምርት ጥራቱን ያለጠበቀ ከመሆኑም በላይ ዋጋው ከሌሎች ነጋዴዎች ጋር ተመሳሳይና የሚጨምርም እንዳላ ተናግረዋል፡፡

" በየዓመቱም የሚገኘው ትርፍ እየቀነሰ በመምጣቱና  ገበያውን በማረጋጋት ረገድ የተጣለበትን አደራ አልተወጣም፤ በዚህም ተጠቃሚ እያደረገን አይደለም" ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል ፡፡

የዩኒየኑ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሰይድ መሃመድ በበኩላቸው የዩኒየኑ ዓላማ እንዲያሳካ አባላት  በመደገፍና በማገዝ በባለቤትነት ስሜት እየሰሩ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

" የአርሶ አደሩን ምርት በተሻለ ዋጋ በመግዛት ለሀገር ዉስጥና ውጭ ገበያ በማቅረብ ገበያውን የማረጋጋትና አባላቱን ተጠቃሚ ለማድረግ ቢታሰብም እቅዱን ማሳካት አልቻልንም " ብለዋል፡፡

ለዚህም የህገ ወጥ ነጋዴዎች መበራከት፣ ፋብሪካዎች ከዩኒየኑ ይልቅ ለአከፋፋዮች ምርታቸውን ቅድሚያ መስጠትና የአባላት ምርት ጥራት መጓደል በምክንያትነት ጠቅሰዋል።

ዩኒየኑ ለሀገር ዉስጥና ውጭ ገበያ ለማቅረብ  ፍቃድ ቢያወጡም በገበያ አለመረጋጋትና በጥራት ችግር ለኪሳራ መደረጋቸውን ተናግረዋል።

ሰብሳቢው  ለዚህም በማሳየነት ያቀረቡት  4 ሺህ ኩንታል የማሾና የቦለቄ ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ኩንታሉነ ቦለቄ በአንድ ሺህ 520 ብር ከአባላቱ ከተገዛ በኋላ በጥራት መጓደል ምክንያት ከኩንታል እስከ 300 ብር ከስረው መሸጣቸው ነው፡፡

በ2009 ዓ.ም. ዩኒየኑ ባደረገው የግብይት እንቅስቃሴ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ በማትረፍ ለአባላቱ ያከፋፈለ ቢሆንም ባለፈው ዓመት 700 ሺህ ያልሞላ ትርፍ መገኘቱን አመልክተዋል።

"ቀጣይ ከባለድርሻ አካላትና አባላቱ ጋር በመነጋገር የተሻለ ግብይት በመፈፀም ገበያውን በማረጋጋትና አባላቱንም ተጠቃሚ ለማድረግ ይሰራል" ብለዋል።

ዩኒየኑ  በደሴ ከተማ በተሰጠው ቦታ ላይ ቢሮና መጋዝን በመስራት በዓመት ለኪራይ የሚያወጣውን አንድ ሚለዮን 500ሺህ ብር ወጪ በማስቀረትም የካፒታል አቅሙን ለማሳደግ  እንዲያግዝው ይደረጋል ተብሏል።

ዩኒየኑ ከሚሰጣቸው ሁለገብ አገልግሎት መካከል ለአባላት የምርት  ማሳደጊያ ግብአትና  ልዩ ልዩ የፍጆታ ሸቀጦችን ማቅረብ፣ ገበያን ማረጋጋትና ትስስር መፍጠር ይገኙበታል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ህብረት ስራ ማህበራት ማስፋፊያ ተጠሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ተወካይ አቶ ሽፈራዉ አያሌው " ዩኒየኖችን በመደገፍና ችግሮችን በውይይት እንዲፈቱ በማድረግ ለአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት እንሰራለን "ብለዋል፡፡

በበ1997ዓ.ም. የተቋቋመው የእሪኩም ሁለገብ  የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን 160ሺህ ያህል  አባላትን ያቀፉ 106 መስረታዊ የህብረት ስራ ማህበራትና 22ሚሊዮን ብር የሚጠጋ  ካፒታል እንዳሉት ተመልክቷል

በደቡብ ወሎ ዞነ እሪኩምን ጨምሮ ሶስት ሁለገብ የህብረት ስራ ዩኒየኖች እንደሚገኙ  ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም