በአፋር ክልል የሶማሌ ማህበረሰብ የሚኖሩባቸው ልዩ ቀበሌዎች የተከሰተው ችግር በውይይት እንዲፈታ ተጠየቀ

91

ጅግጅጋ  ጥር 10/2011 በአፋር ክልል የሶማሌ ማህበረሰብ የሚኖሩባቸው ልዩ ቀበሌዎች የተከሰተው የፀጥታ ችግር በውይይት እንዲፈታ የሶማሌ አገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች በሰላማዊ ሰልፍ ጠየቁ።

ሰላማዊ ሰልፈኞቹ ዛሬ በጅግጅጋ ከተማ ባደረጉት ትዕይን ሕዝብ እንዳመለከቱት ልዩ ቀበሌዎች ነዋሪዎች የማንነት ጥያቄ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ጠይቀዋል።

በአፋርና በሶማሊ ክልሎች አዋሳኝ ቀበሌዎች በተከሰተው ግጭት ሕይወታቸው ላጡ ዜጎች የተሰማቸውን ኅዘን ገልጸዋል።

በሰልፉ ላይ ከተካፈሉት አገር ሽማግሌዎች መካከል ሱልጣን ፉዚ መሐመድ እንዳሉት የሁለቱ ክልሎች ሕዝቦች የቅርብ ዝምድና ያላቸው፣ ለዘመናት አብሮ የኖሩና  የጋራ እሴቶችን እንደሚጋሩ አስታውሰው፣በልተገባ መንገድ ወደ ግጭት የሚያስገባቸው አካላት በሕግ ሊጠየቁ ይገባል ብለዋል።

ሱልጣን አብዲራህማን በዴ የተባሉ የአገር ሽማግሌ በበኩላቸው የፌዴራል፣የአፋርና የሶማሌ ክልሎች የማህበረሰቡን ደህንነት ለማስጠበቅ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጠይቀዋል።

አቶ መሐመድ አደን የተባሉ የሰላማዊ ሰልፍ ተካፋይ በበኩላቸው በሁለቱ ሕዝቦች መካከል እየተፈጠረ ያለውን ግጭት ለማስቆም ሁሉም አካላት ለውይይት ቅድሚያ እንዲሰጡ አሳስበዋል።

ሰልፈኞቹ ''የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕዝቡን ሕገ መንግሥታዊ የማንነት ጥያቄ በአስቸኳይ እንዲያስከብር እንጠይቃለን!''፣ ''ችግሩ በውይይት እንዲፈታ እንፈልጋለን!"ና  ''የችግሩ ፈጣሪዎች ለሕግ መቅረብ አለባቸው!'' የሚሉ  መፈክሮችን ይዘው ነበር።

በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እንዲጠቃለሉ የተደረጉት አዳይቱ፣ ኦንዱፎ፣ ገርበ ኢሲና ገዳማይቱ የተባሉ ከተሞችና አካባቢያቸው ናቸው።

ከተሞቹ ከጂቡቲ ወደ አዲስ አበባ በሚወስደው አስፋልት መንገድ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም