ቀጥታ፡

የአፋር ክልል አርብቶ አደሮች 54ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ እያለሙ ነው

ሰመራ ጥር 10/2011 የአፋር ክልል አርብቶ አደሮችን ሕይወት ለመለወጥ ከእንስሳት እርባታው በተጓዳኝ 54ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ እየለማ መሆኑን የክልሉ የክልሉ እንስሳት፣ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ገለጸ።

የአፋር ክልል አርብቶ አደሮች ቀን ለዘጠነኛ ጊዜ ዛሬ በአፋምቦ ወረዳ ተከብሯል።

የቢሮው ኃላፊ  አቶ ዓሊ ሁሴን በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የክልሉን አርብቶ አደሮች ሕይወት ለመቀየር እየተደረገ ባለው ጥረት አርብቶ አደሮቹ ውሃማ አካላትን ተጠቅመው ወደ እርሻ ሥራ ገብተዋል።

ሥራው የሚከናወነው የክልሉ መንግሥት የአርብቶ አደሩን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋጋጥ  የአዋሽ ወንዝና የከርሰምድር ውሃ አማራጮችን መጠቀም በሕይወታቸው ለውጥ ለማምጣት ባደረገው እንቅስቃሴ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዚህም በሰብል፣በጓሮ አትክልትና በቅባት እህል ምርት የሚሰማሩ አርብቶ አደሮች የሚያደርጉት ተሳትፎ  ዕድገት እያሳየ መምጣቱን  ገልጸዋል።

በተለይ አርብቶ አደሩ የእንስሳት ሃብት ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኝ በክልል ደረጃ ከሚለማው 700 ሄክታር የመኖ ልማት በተጨማሪ በወረዳዎች ልማቱ እየተስፋፋ መሆኑን አቶ ዓሊ አስረድተዋል።

በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ የግብርና ኤክስቴንሽን ሠራተኞችና አጋር የልማት ድርጅቶች ልማቱን ለማጠናከር የአርብቶ አደሩን ሕይወት ለመቀየር የተጀመረውን እንቅስቃሴ እንዲያጠናክሩት ኃላፊው ጠይቀዋል።

የአፋምቦ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሁሴን ዓሊ በወረዳው ቀን መከበሩ የወረዳው አርብቶ አደሮች ከሌሎች ወረዳዎች አቻዎቻቸው ጋር ተሞክሯቸዉን ለመለዋወጥና እርስ-በርስ ለመማማር ዕድል እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።

በወረዳው የሁመዶይታ ቀበሌ ሞዴል ከፊል አርብቶ አደር አቶ ከቢር  ጀይላኔ ባላቸው 1 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ አፕል፣ማንጎንና ቴምርና ቋሚ ተክሎችን ጨምሮ የጓሮ አትክልት በማልማት የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጣቸው በላይ፤ በዓመት ከ100ሺህ ብር በላይ ገቢ እንደሚያገኙ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በሚደረግላቸዉ ድጋፍ በዚህ ዓመት ሱፍ በማልማት ኑሮአቸውን ለማሻሻልና ገቢያቸውን ለማሳደግ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

ከእዋ ወረዳ ሂዳ ቀበሌ የመጡት ሞዴል ከፊል አርብቶ አደር ወይዘሮ ፋጡማ አብዱልቃር በላቸው ሁለት ሄክታር መሬት የጓሮና ቋሚ አትክልት በማልማት ሰባት ልጆቻቸውን ለከፍተኛ ትምህርት ማብቃታቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይ የክልሉ መንግሥት ያለባቸውን የዉሃ አጥረትና የቋሚ ተክሎችና የጓሮ አትክልት ምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረት ከፈታላቸው የእርሻ ሥራቸውን በማስፋፋት ውጤታማ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

በበዓሉ ሞዴል አርብቶ አደሮችን የሚያካትቱ  79 ባለድርሻ አካሎች የእውቅና ሰርተፍኬትና ዋንጫ ተበርክቶላቸዋል።

በዓሉ በክልሎችም  ሆነ በአገር ደረጃ  የልማት ተሞክሮዎችን በማስፋት የአርብቶ አደሩን ሕይወት ለማሻሻል ትኩረት የሚሰጥበት ነው።

የኢትዮጵያ አርብቶ አደሮች ቀን ለ17ኛ ጊዜ ከጥር 15-17/2011በደቡብ ኦሞ ዞን ርዕሰ ከተማ በጂንካ ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም