በመቀሌ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች የተሳተፉበት አገር አቀፍ አውደ ርዕይ ተከፈተ - ኢዜአ አማርኛ
በመቀሌ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች የተሳተፉበት አገር አቀፍ አውደ ርዕይ ተከፈተ
መቀሌ ግንቦት 18/2010 በመቀሌ ከተማ ከ200 በላይ አነስተኛ፣ መካከለኛና ትላልቅ የማኑፋክችሪንግ ኢንዱስትሪዎች የተሳተፉበት አገር አቀፍ አውደ ርዕይ ተከፈተ፡፡ አውደርዕዩን የትግራይ ክልል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ኤጀንሲ፣ የኢትዮጵያና የክልሉ አሠሪዎች ፌዴሬሽን በጋራ ያዘጋጁት መሆኑም ተገልጿል፡፡ የትግራይ ክልል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክችሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ መሀሪ ገብረሚካኤል እንዳሉት አውደ ርዕዩ የፈጠራ ባለሙያዎችና አምራች ኢንዱስቱሪዎች ምርቶቻቸውን እንዲያስተዋውቁ በማድረግ በኩል ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ ከትናንት ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው በእዚህ አውደርዕይም ከ200 በላይ አነስተኛ፣ መካከለኛና ትላልቅ የማኑፋክችሪንግ ኢንዱስትሪዎች መሳተፋቸውን አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ እንግዳ እሸቴ በበኩላቸው "ሰላም የሰፈነበት የኢንዱስትሪ ልማት በአገራችን እውን ለማድረግ ከሠራተኞች ጋር በቅንጅት ይሰራል" ብለዋል፡፡ አውደ ርዕዩ ኢንተርፕራይዞች የሚያጋጥማቸውን የገበያ ትስስር ከመፍታት ባለፈ ምርታቸውን ለተጠቃሚዎች ለማስተዋወቅ እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል። በአውደ ርዕዩ ከተሰተፉ ኢንተርፕራይዞች መካከል በጨርቃጨርቅ ሥራ የተሰማሩት አቶ ኑረዲን ስኢድ አንዱ ናቸው፡፡ እሳቸው እንዳሉት መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት በ500 ብር ከጀመሩት የልብስ ስፌት ሥራ ተላቅቀው በአሁኑ ወቅት ወደ ባለሃብትነት መሸጋገር ችለዋል፡፡ በሦስት ሚሊዮን ብር የተገዙ ሃያ ዘመናዊ የልብስ ስፌት ማሽን ባለቤት ከመሆን ባለፈ ለሃያ ሰዎች የሥራ እድል መፍጠራቸውን የገለጹት ባለሀብቱ፣ አውደርዕዩ የገበያ ትስስር ይፈጥርልኛል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል። የቤተሰብ ጥገኛ ከመሆን ተላቆ ከሁለት ዓመት በፊት ከማይጨው ችፑድ ፋብሪካ ተረፈ ምርት በመጠቀም የሚያመርተውን የቡና ሲኒ ረከቦት ወደ ተለያዩ ክልሎች በመላክ እንደሚያከፋፍል ገልጾ፣ አውደርዕዩ “ምርቴን በቀላሉ ለማስተዋወቅ ያግዘኛል፤ ከሌሎች ጋር የገበያ ትሰስርም ይፈጥርልኛል" ብሏል። እንደወጣቱ ገለጻ፣ መንግስት ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በሰጠው ትኩረት ለራሱ ሥራ ከመፍጠር ባለፈ ለ16 ወጣቶችም ቋሚ የሥራ ዕድል ፈጥሯል። በትንሽ ገንዘብ የጀመረው ሥራም በአሁኑ ወቅት የግማሽ ሚሊዮን ብር ካፒታል ባለቤት እንዳደረገው ገልጿል፡፡