በፕሪሚየር ሊጉ 11ኛ ሣምንት መርሃ ግብር መከላከያና ስሑል ሽረ አቻ ወጡ - ኢዜአ አማርኛ
በፕሪሚየር ሊጉ 11ኛ ሣምንት መርሃ ግብር መከላከያና ስሑል ሽረ አቻ ወጡ
አዲስ አበባ ጥር 10/2011 በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 11ኛ ሳምንት መርሃ ግብር መከላከያና ስሑል ሽረ ሁለት አቻ በሆነ ውጤት ተለያዩ።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ዛሬ 11፡00 ሠዓት ሊካሄድ የነበረ ቢሆንም በከተራ በዓል ምክንያት ከረፋዱ 4፡00 ሠዓት ተደርጓል።
ጨዋታው ተጀምሮ አንድ ደቂቃ ሳይሞላው እንግዳው ቡድን ስሑል ሽረ በአጥቂው ልደቱ ለማ አማካኝነት ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።
ለግቡ መቆጠር የመከላከያው ግብ ጠባቂ ይድነቃቸው ኪዳኔ ስህተት አስተዋጽኦ አድርጓል።
ከግቡ መቆጠር በኋላ የተነቃቁት ስሑል ሽረዎች ወደ መከላከያ ግብ ክልል በተደጋጋሚ የደረሱ ሲሆን ግቡን ያስቆጠረው ልደቱ ለማ ከመከላከያው ግብ ጠባቂ ይድነቃቸው ኪዳኔ ጋር ተገናኝቶ የሳተው ኳስ ተጠቃሽ ነው።
መከላከያ በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ተወስዶበት ከነበረው ብልጫ በኋላ በቀሪው ጊዜ ተጭኖ ለመጫወት ጥረት ያደረገ ሲሆን ያገኛቸውን የግብ እድሎች መጠቀም አልቻለም።
የመከላከያ የፊት አጥቂዎች ፍጹም ገብረማርያምና ምንይሉ ወንድሙ፤ የክንፍ ተጫዋቹ ዳዊት ማሞ ቡድኑን አቻ ለማድረግ የሚያስችሉ የግብ አጋጣሚዎችን ቢያገኙም ኳስ ከመረብ ማሳረፍ አልቻሉም።
ቴዎድሮስ ታፈሰ፣ ሳሙኤል ታዬና አምበሉ ሽመልስ ተገኝ ለመከላከያ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን አድርገዋል።
በማጥቃት እንቅስቃሴው የቀጠለው መከላከያ በ32ኛው ደቂቃ ምንይሉ ወንድሙ ያሻገረውን ኳስ ፍጹም ገብረማርያም ወደ ግብ በመቀየር ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።
ከግቡ መቆጠር በኋላ መከላከያ ጨዋታውን መምራት የሚችልባቸውን እድሎች መጠቀም አልቻለም፤ ሲሳቱ የነበሩ ኳሶችም ያለቀላቸው ነበሩ።
ከእረፍት መልስ ባለሜዳው መከላከያ በማጥቃት እንቅስቃሴው በመቀጠል ተደጋጋሚ የግብ እድሎችን ቢያገኝም ፍጹም ገብረ ማርያምና ምንይሉ ወንድሙ ወደ ግብ መቀየር አልቻሉም።
62ኛው ደቂቃ ላይ መከላከያዎች ወደ ስሑል ሽረ የግብ ክልል በመግባት ተቀይሮ የገባው አጥቂ ፍቃዱ አለሙ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሃፍቶም ቢሰጠኝ ሲመልሰው በቅርብ ርቀት ላይ የነበረው ፍጹም ገብረማርያም ኳሱን ከመረብ በማሳረፍ ቡድኑን መሪ አድርጎታል።
ግቡ ከተቆጠረ በኋላ የስሑል ሽረ የአሰልጣኝ ቡድን ፍጹም ገብረማርያም ግቡን ሲያስቆጥር ከጨዋታ ውጭ ነበር በሚል በዳኞች ላይ ተቃውሞ አቅርቧል።
መከላከያ ግቡን ካስቆጠረ በኋላም መሪነቱን የሚያሰፋበት የሚችልባቸውን አጋጣሚዎች ቢያገኝም አልተጠቀመባቸውም።
የመከላከያው የመሐል ተጫዋች ፍሬው ሰለሞን የመታውን ኳስ በረኛው መልሶት ፍጹም ገብረማርያም አስቆጥሮ የነበረ ሲሆን ፌዴራል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ሽረውታል፤ ረዳት ዳኛው ባንዲራ አለማውጣታቸውም ውዝግብ ፈጥሮ ነበር።
የመከላከያ በርካታ እድሎችን ማምከን በጨዋታው ላይ እንዲቆይ ያደረገው ስሑል ሽረ ተቀይሮ የገባው ኪዳኔ አሰፋ በ76ኛው ደቂቃ ከፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውጭ አክርሮ የመታት ኳስ ከመረብ አርፋ እንግዳውን ቡድን አቻ አድርጋዋለች።
ስሑል ሽረዎች በዚህ በመነቃቃት ወደ መከላከያ የግብ ክልል በመድረስ በኪዳኔ አሰፋና በልደቱ ልማ የግብ እድሎችን ቢፈጥርም ጎል ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተው ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ባለ ሜዳው ቡድን መከላከያ ጨዋታውን ለማሸነፍ ከበቂ በላይ የግብ እድል ቢፈጥርም መጠቀም አለመቻሉ ዋጋ አስከፍሎታል።
በጨዋታው የስሑል ሽረዎቹ ጅላሎ ሻፊና አብዱሰላም አማን ቢጫ ካርድ ተመልክተዋል።
የመከላከያው አሰልጣኝ ስዩም ከበደ 'በጨዋታው ያገኘነው ውጤት አይገባንም ብዙ የግብ እድሎች አምክነን አቻ በመውጣታችን በጣም አዝኛለሁ' ብለዋል።
በቅዱስ ጊዮርጊስ ከደረሰብን የ5 ለ 1 ሸንፈት በኋላ ከነበረው ስሜት ለመውጣትና ለማሸነፍ ጠንካራ ዝግጅት አድርገን ለዛሬው ጨዋታ ተዘጋጅተን ነበር ሊሳካ አልቻለም ነው ያሉት።
የአጨራረስ ድክመቱ ከአጥቂዎቹ ብቃት ጋር የተያዘዘ በመሆኑ ይህን አርመን በቀጣይ ጨዋታ 'እንመጣለን' ያሉት አሰልጣኙ በጉዳትና በቅጣት የሌሉ ተጫዋቾች ሲመለሱ ግብ የማስቆጠር ችግሩ ይፈታል ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል።
የስሑል ሽረው አሰልጣኝ ዳንኤል ጸሃዬ የመጀመሪያው ግብ ከተቆጠረ በኋላ 'ተጫዋቾቼ ወደ ኋላ አፈግፍገው መጫዋታቸው ለተጋጣሚው ቡድን ኳን ይዞ እንዲጫወትና የግብ እድል እንዲፈጥር አድርጓል' ብለዋል።
በዚህ ምክንያት ግብ ሊቆጠርባቸው እንደቻለም ተናግረዋል።
ከእረፍት መልስ የተሻለ እንቅስቃሴ ለማድረግ እንደቻሉና የመከላከያ ግብ አለማስቆጠር በጨዋታው እንዲቆዩ በማድረጉ ያገኙትን እድል ወደ ግብ በመቀየራቸው አቻ መውጣታቸውንም አክለዋል።
ውጤቱንም ተከትሎ መከላከያ በዘጠኝ ነጥብ 12ኛ ደረጃ ሲይዝ ስሑል ሽረ በሰባት ነጥብ ከነበረበት 14ኛ ወደ 13ኛ ደረጃ ከፍ በማለት ከወራጅ ቀጠና ወጥቷል።
ዛሬ በጎንደር ስታዲየም በተደረገ የ11ኛ ሳምንት ጨዋታ ፋሲል ከተማ ወላይታ ድቻን 1 ለ 0 በሆነ ውጤት ያሸነፈ ሲሆን ውጤቱንም ተከትሎ ደረጃውን ከ6ኛ ወደ 3ኛ ከፍ አድርጓል።
የፕሪሚየር ሊጉ 11ኛ ሳምንት ጨዋታ ከነገ በስቲያ ሲካሄድ በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ደደቢት ከአዳማ ከተማ ከቀኑ በዘጠኝ ሠዓት ይጫወታሉ።
የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ ቡና በ22 ነጥብ ሲመራ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስና ፋሲል ከተማ በተመሳሳይ 18 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል 2ኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
ጅማ አባ ጅፋር፣ ደቡብ ፖሊስና ደደቢት ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ የሊጉ ግርጌ ላይ ተቀምጠዋል።
የኮከብ ጎል አግቢነቱን የአዳማው ዳዋ ሁቴሳና የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ በተመሳሳይ 7 ግቦች ሲመሩ፣ የመከላከያው ምንይሉ ወንድሙ በ6 የሃዋሳ ከተማዎቹ እስራኤል እሸቱና ታፈሰ ሰለሞን በተመሳሳይ 5 ግቦች ይከተላሉ።