በነቀምቴ ከተማ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጀመረ

110

ነቀምቴ   ጥር 10/2011 በነቀምቴ ከተማ አስተዳደር  ከ87 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የሚካሄዱ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጀመረ፡፡

ግንባታው  የተጀመረው  የከተማ አስተዳደሩ የምክር ቤት አባላት፣የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት ትናንት ነው፡፡

የፕሮጀክቶቹ ግንባታ ከዓለም ባንክ ፣ከክልሉ መንግሥት ፣ከአስተዳደሩ ማዘጋጃ ቤትና ከሌሎችም የገቢ ምንጮች በተገኘ ገንዘብ ወጪ የሚካሄድ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ቦጋለ ሹማ ስራ በተጀመረበት ስነስርዓት ወቅት ገልጸዋል፡፡

በአካባቢው ተፈጥሮ በነበረው አለመረጋጋት ምክንያት ቀደም ብለው መጀመር የነበረባቸው የልማት ፕሮጀክቶች ላለፉት ስድስት ወራት  ወደ ኋላ  መቅረታቸውን አመልክተዋል፡፡

አሁን አካባቢው በተፈጠረው አንፃራዊ ሠላም  በመጠቀም የተለያዩ የህብረተብ ክፍሎች በተገኙበት ግንባታ መጀመሩን የገለጹት ከንቲባው ስራው በስኬት ተጠናቆ ለህብረተሰቡ አገልገሎት እንዲበቃ የከተማው ነዋሪ ሕዝብ ከአስተዳደሩ ጎን በመቆም  የድርሻውን እንዲወጣም  አሳስበዋል፡፡

ከልማት ፕሮጀክቶቹ መካከል የከተማው ውስጥ ለውስጥ የድንጋይ ንጣፍ መንገድ ፣የጎርፍ መውረጃ ቦዮች፣  የዋናው መንገድ የመብራትና የንጹህ መጠጥ ውሃ  መስመር ማስፋፋትና የቁጠባ ቤቶች ግንባታ ይገኙበታል፡፡

የከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሳዲያ አህመድ በበኩላቸው የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች የጥራት ደረጃቸውን ጠብቀው  በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ  የተጠናከረ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡

በየደረጃው የሚገኘው አመራርና ህብረተሰቡም  ለግንባታው መሳካት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ አሳስበዋል ፡፡

ስራው ሲጀመር በነበረው ስነስርዓት ከተገኙት መካከል የከተማው ቀበሌ ሰባት ነዋሪና  የሀገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ ወጋሪ ከንዶ የፕሮጀክቱ ግንባታ ያለምንም ችግር እንዲካሄድ ህብረተሰቡን ለማስተባር ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም