ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ለግጭት መንስኤ የሚሆኑ አስተሳሰቦችን በጋራ መከላከል እንደሚገባ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ለግጭት መንስኤ የሚሆኑ አስተሳሰቦችን በጋራ መከላከል እንደሚገባ ተጠቆመ
ሶዶ ጥር 10/2011 በሶዶ ከተማ ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ለግጭት መንስኤ የሚሆኑ አስተሳሰቦችን የሚያራምዱ አካላትን የከተማዋ የሃይማኖት ተቋማት በጋራ ተቀናጅተው ሊከላከሉ አንደሚገባ ተጠቆመ።
የሶዶ ከተማ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሃይማኖቶች መካከል ሊኖር ስለሚገባው መከባበር ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ አካሂዷል፡፡
ከሶዶ ከተማ የአራዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ተወካይ መላከ ገነት ብርሃኑ መኮንን እንዳሉት የሁሉም ነገሮች መሰረት የሆነውን ሰላም መስበክ የሁሉም እምነት ተቋማት ሚና ነው፡፡
"አንዳንድ ግለሰቦች አሁን ያለውን ሀገራዊ የፖለቲካ ለውጥ እንደምቹ አጋጣሚ ተጠቅመው የግል ፍላጎታቸውንና ተልእኳቸውን ለማሳካት ሃይማኖትን መጠቀሚያ የማድረግ አዝማሚያ ይስተዋልባቸዋል" ብለዋል፡፡
የእምነት ተቋማት ለተከታዮቻቸው ተገቢና ተከታታይ ትምህርት በመስጠት ያልተገባ አስተሳሰብ የሚያራምዱትን መከላከል እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡
"በእምነት ስም የሌሎችን ሃይማኖቶች መዝለፍ እና እርስ በርስ የመከባበር እሴትን ወደ ጎን በመተው የሚፈጸም ስብከትም ሆነ አስተምህሮን ለመከላከል የሃይማኖት ተቋማት በቅንጅት መስራት ይኖርብናል " ብለዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ-ክርስትያን መካነ-ኢየሱስ የሶዶ ማህበረ-ምዕመናን ተወካይ አቶ ማደቦ ማና በሃይማኖቶች መካከል ልዩነት ለመፍጠር የሚደረግ እንቅስቃሴ ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአካባቢው በሃይማኖት ተከታዮች መካከል በሃሳብ ልዩነት የሚቀሰቀሱ ግጭቶች በመዛመትና ጎራ በመፍጠር ስጋት እያስከተሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ ነገሮችን በእርጋታ ማየትና የግለሰቦችን ፍላጎት ለማሳካት ከወንድሙና እህቱ ጋር በመቃቃር ለሰላም መደፍረስ ምክንያት እንዳይሆን አስገንዝበዋል፡፡
"የሃይማኖት ተቋማትና መሪዎች ሃይማኖቶችን በእኩል ማየት፣ ለህዝቡ የሚበጀውን ማሰብና ሃይማኖታዊ ዕሴቶች ሳይሸራርፉ የመጠበቅ ኃላፊነት አለብን" ብለዋል፡፡
በአካባቢው የተረጋገጠ ሰላም ለማስፈን የኑሮ ዜይቤ ላይ ያተኮረ ሳምንታዊና ዕለታዊ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት እየሰሩ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የወላይታ ዞን እስልምና ሃይማኖት ሥራ አስፈጻሚ አባል ሸኽ ጁሃር ሃምድ ናቸው፡፡
"የትኛውንም ሃይማኖት ለማራመድም ሆነ ለማስፋት ሰላም ወሳኝ ነው" ያሉት ሸኽ ጁሃር፣ ህብረተሰቡም ሆነ የሃይማኖት አባቶች የሌሎችን እምነት ሊያከብሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የሶዶ ከተማ የሃይማኖት ተቋማት ፎረም ምክትል ሰብሳቢ አባ ብሩክ የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች ተቀራርበው መስራታቸው ችግሮች ሲከሰቱ በጋራ መፍትሄ ለመስጠት ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡
ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ለጸጥታ መደፍረስ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ምልክቶች እየታዩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
የምክክር መድረኩም ችግሩን ከእንጭጩ ለማስወገድና ተቋማቱ በአፍራሽ አስተሳሰቦች ላይ ግንዛቤ ኖሯቸው ተከታዮቻቸውን እንዲያስተምሩ ለማድረግ ታስቦ መዘጋጀቱንም አስረድተዋል፡፡
አባ ብሩክ እንዳሉት የአምልኮ ቦታዎች መጠጋጋት፣ የጎዳና ላይ ስብከቶች፣ ሌሎች ሃይማኖቶችን የሚተነኩስ ቅስቀሳዎች፣ እንዲሁም ከነበሩበት ቤተ-ዕምነት አፈንግጦ የራስን ለመመስረት የሚፈልጉ አካላት መበራከት ከተስተዋሉ ችግሮቹ መካከል በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡
"ማንኛውም ሰው የራሱን ዕምነትና ሃይማኖት በፈለገው መልኩ ለማራመድ መብት ቢኖረውም ህግንና የሌሎችን መብት በጣሰ መልኩ መሆን የለበትም" ብለዋል፡፡
የሃይማኖት ተቋማትና መሪዎቻቸው የፍቅር፣ የመከባበርና የአብሮነት ዕሴቶችን በማጎልበት ለሰላምና ለልማት ቅድሚያ በመስጠት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አባ ብሩክ አስገንዝበዋል፡፡
በወላይታ ሶዶ ከተማ ሰባት የተለያዩ ሃይማኖቶችና ከ40 የሚበልጡ ቤተ-ዕምነቶች እንደሚገኙ የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው።