ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ የከተራ በዓል ተከበረ

አዲስ አበባ ጥር 10/2011 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ የከተራ በዓል ተከብሯል።

ከተራ ''ከተረ'' ከሚለው የግዕዝ ቃል የተወሰደ ሲሆን ትርጉሙም ''ውሃ መክበብ'' ወይም ''መገደብ''ማለት ነው።

በዓሉ ከጥምቀት በዓል አንድ ቀን ቀድሞ ነው የሚከበረው።

የጥምቀት ዋዜማ ታቦተ-ሕጉ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ውሃ ባለበት አካባቢ ስለሚያድር የየአጥቢያው የእምነቱ ተከታይ በአንድ ላይ በወንዝ ዳር ወይም በምንጭ አካባቢ ድንኳን ይተከላል፤ የወንዝ ወይም የምንጭ ውሃም ይገደባል፤ ይከተራል።

ይህ በጥምቀት ዋዜማ የሚደረገው ውሃውን የመከተርና የመገደብ ስርዓትም ''ከተራ'' የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡

የታሪኩ መነሻ መዝሙር 113 ቁጥር አምስት ላይ በመጽሃፍ ቅዱስ የተጻፈው ነው ያሉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የአዲስ አበባ አገረ ስብከት የቅዱስ ፓትሪያርኩ ረዳት ሊቀ-ጳጳስ ዶክተር አቡነ አረጋዊ ''ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ መሃል ላይ ሲቆም ባህር ባህር አይታ ሸሸች የሚለውን ቃል መነሻ በማድረግ ነው ብለዋል።

በዚህ መነሻነት ታቦታቱ ከየማደሪያቸው ወጥተው በውሃ ዳር በተዘጋጀ ቦታ ማክበር ከጀመሩ ከሁለት ሺህ ዓመታት በላይ ማስቆጠራቸውንም  ዶክተር አቡነ አረጋዊ ለኢዜአ ገልጸዋል።

የተጠራቀመው ውሃ በማግሥቱ ጥር 11 ቀን የጥምቀት በዓል ሲከበር የህዝቡ መጠመቂያ ይሆናል። ከተራ በተለያዩ አካባቢዎች በተለይ በአክሱም የንግሥት ሳባ መዋኛ (ማይ ሹም)፣ በጎንደር የአፄ ፋሲል መዋኛ፣ በላስታ የላሊበላ መዋኛ፣ በሸዋ የአፄ ዘርዓያዕቆብ ፍርድ መስጫ አደባባይ፣ በአዲስ አበባ ደግሞ ጃንሆይ ሜዳ (ጃንሜዳ) በደማቅ ስነ-ስርዓት ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም