ጅማ አባ ጅፋር ነገ ምሽት ከሞሮኮ አቻው ጋር የመልስ ጨዋታውን ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
ጅማ አባ ጅፋር ነገ ምሽት ከሞሮኮ አቻው ጋር የመልስ ጨዋታውን ያደርጋል
አዲስ አበባ ጥር 10/2011 ጅማ አባ ጅፋር የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ 2ኛ ዙር የመልስ ጨዋታውን ነገ ምሽት ከሞሮኮው ሀሳኒያ ዩ ኤስ አጋዲር ጋር ያደርጋል።
ጨዋታው 45 ሺህ 480 ተመልካች በሚያስተናግደው በስታድ አድራር አጋዲር ስታዲየም ነው የሚካሄደው።
ጥር 5 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ሀሳኒያ ዩ ኤስ አጋዲር 1 ለ 0 ማሸነፉ ይታወቃል።
በዚህ ውጤት ሀሳኒያ ዩ ኤስ አጋዲር ወደ ምድብ ድልድል የመግባት እድሉን ያሰፋ ሲሆን በአንጻሩ ጅማ አባ ጅፋር በሜዳው በመሸነፉ እድሉን አጥብቧል።
ጅማ አባ ጅፋር ወደ ምድብ ድልድሉ ለመግባት ተጋጣሚውን በሁለት ጎል ልዩነት ማሸነፍ ይጠበቅበታል።
በአፍሪካ አህጉራዊ የክለብ ውድድሮች ምክንያት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን በተቆራረጠ መልኩ እያደረገ ያለው ጅማ አባ ጅፋር በሊጉ እስካሁን ስድስት ጨዋታዎችን አድርጎ በስድስት ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ክለቡ የሊጉን ጨዋታዎች ወጥነት ባለው መልኩ አለማካሄዱ በሊጉ አጀማመር ላይ ተጽእኖ አሳድሮበታል ማለት ይቻላል።
ጅማ አባ ጅፋር በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ መሳተፍ የቻለው የግብጹ አል አህሊ ከአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ በደርሶ መልስ ውጤት መሰናበቱን ተከትሎ ነው።
በአሰልጣኝ ዘማሪያም ወልደ ጊዮርጊስ የሚመራው ጅማ አባ ጅፋር የነገውን ጨዋታ ለማድረግ ትናንት ምሽት ወደ ስፍራው አቅንቷል።
የሱሳ አጋዘን የሚል ስያሜ ያለው የሞሮኮው ሃሳኒያ ዩ ኤስ አጋዲር ክለብ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ሲሳተፍ የዘንድሮው ሁለተኛ ጊዜው ነው።
በአርጀንቲናዊው አሰልጣኝ ሚጉዌል አንጌል ጋሞንዲ የሚመራው ሃሳኒያ ዩ ኤስ አጋዲር በአዲስ አበባ ስታዲየም ያስመዘገበውን ድል ተከትሎ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ምድብ ድልድሉ ለመግባት ያለውን እድል አስፍቷል።
የጅማ አባ ጅፋርና ሃሳኒያ ዩ ኤስ አጋዲርን ጨዋታ አልጄሪያዊው ኢንተርናሽናል ዳኛ ናቢል ቡካልፋ በመሐል ዳኝነት ይመሩታል።
ከቻምፒየንስ ሊጉ አንደኛ ዙር የወደቁ 15 ክለቦችን በኮንፌዴሬሽን ዋንጫው አንደኛ ዙር ካለፉ ክለቦች ጋር የሚያገናኘው የሁለተኛ ዙር ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጨዋታ ወደ ምድብ ድልድሉ የሚገቡ 16 ክለቦችን የሚለይ ይሆናል።
በሌላ በኩል በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ሁለተኛ ዙር የመልስ ጨዋታ ነገ የደቡብ አፍሪካው ካይዘር ቺፍስ ከዛምቢያው ዜስኮ ዩናይትድ የሚያደርጉትን ጨዋታ ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ በመሐል ዳኝነት ይመራዋል።
ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኞች ተመስገን ሳሙኤልና ኃይለራጉኤል ወልዳይ ጨዋታውን በረዳት ዳኝነት ይመሩታል።
በሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ ጨዋታ የዛምቢያው ዜስኮ ዩናይትድ በሜዳው 3 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።
በላይ ታደሰ የነገው ጨዋታ በዘንድሮው የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫን ሲዳኝ ሁለተኛው ሲሆን የዴሞክራቲክ ኮንጎው ኤኤስ ንዩኪ እና የአንጎላው ፔትሮ ሉዋንዳን ያደረጉትን የመጀመርያ ዙር ጨዋታ ማጫወቱ ይታወሳል።