የምርጫ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው አቶ ተስፋዬ ካህሳይ በእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዲወዳደሩ ወሰነ - ኢዜአ አማርኛ
የምርጫ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው አቶ ተስፋዬ ካህሳይ በእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዲወዳደሩ ወሰነ
አዲስ አበባ ግንቦት 18/2010 የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ አቶ ተስፋዬ ካህሳይ በምርጫው እንዲወዳደሩ ወሰነ። አስመራጭ ኮሚቴው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንታዊና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት የሚወዳደሩ እጩዎችን ግንቦት 14 ቀን 2010 ዓ.ም ይፋ ሲያደርግ የትግራይ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የወከሉትን አቶ ተስፋዬ ካህሳይ እውቅና በማንሳቱ በምርጫው እንደማይወዳደሩ አሳውቆ ነበር። የምርጫ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው ከግንቦት 15 ቀን እስከ ግንቦት 18 ቀን 2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንታዊና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት እጩዎች ዝርዝር ላይ የቀረቡ ቅሬታዎችን መርምሮ ዛሬ የመጨረሻ ውሳኔ ሰጥቷል። በዚሁ መሰረት የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው የአስመራጭ ኮሚቴውን ውሳኔው ሽሮ አቶ ተስፋዬ ካህሳይ በምርጫው ላይ እንዲሳተፉ ውሳኔ ማሳለፉን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። አቶ ተስፋዬ ከድሬዳዋ ከተወከሉት አቶ ጁነዲን ባሻህ ፣ ከአማራ ከተወከሉት አቶ ተካ አስፋው እና ከኦሮሚያ ከተወከሉት አቶ ኢሳያስ ጂራ ጋር ግንቦት 26 ቀን 2010 ዓ.ም በአፋር ክልል ሰመራ በሚካሄደው የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ምርጫ የሚወዳደሩ ይሆናል። በፕሬዚዳንትነት እጩ ዝርዝር ላይ ኢንጅነር ፀደቀ ይሁኔ እና ኢንጂነር ቾል ቤል ያቀረቡት ይግባኝ በይግባኝ ሰሚ ኮሚቴውም ውድቅ ሆኗል። በተጨማሪም ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው ከዘጠኙ ክልሎችና የሁለቱ ከተማ አስተዳድሮች እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች የተወከሉ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ እንዲወዳደሩ የአስመራጭ ኮሚቴው 22 ይፋ ያደረጋቸው እጩዎች በምርጫው እንደሚሳተፉ አስታውቋል። የቀድሞው የደደቢት ክለብ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል አወል አብዱራሂም ከትግራይ፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አቶ ሰውነት ቢሻው ከአማራ፣ አሰልጣኝ አስራት ሃይሌ ከአዲስ አበባ፣ አቶ አበበ ገላጋይ ከድሬዳዋና አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ ከደቡብ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች በእጩነት ከቀረቡት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እጩዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ። ወይዘሮ ሶፊያ አልማሙ ከቤኒሻንጉል ጉምዝ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አባልነት ምርጫ ብቸኛዋ ሴት ተወዳዳሪ ሆነው ቀርበዋል። የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፊፋ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትና ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ እስከ ግንቦት 26 ቀን 2010 ዓ.ም እንዲከናወን ማሳሰቢያ መስጠቱ የሚታወስ ነው። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ አራት ጊዜ መራዘሙ ይታወቃል።