ቀጥታ፡

በህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ የነበሩ የአሰራር ክፍተቶች ተፈተው ግንባታው እንዲፋጠን ተጠየቀ

አዲስ አበባ ጥር 9/2011  በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ይስተዋሉ የነበሩ የአሰራር ክፍተቶችን መፍትሄ በመስጠት ግንባታው መፋጠን እንዳለበት  ተጠየቀ።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንበታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት በግድቡ ግንባታ ዙሪያ ከተለያዩ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ ላይ ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት የተወከሉ ተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተዋል፤ አስተያየቶችንም ሰንዝረዋል።

በጥያቄያቸውም የባለሙያዎችን ብቃት፣ ለህዝቡ ወቅታዊ መረጃ ያለማድረስ ችግር፣ የግንባታ ጊዜ መጓተትንና የፋይናንስ አጠቃቀም ችግሮችን በሚመለከት አንስተዋል።

ከሴት ነጋዴዎች ማህበር ተወክለው የተገኙት ወይዘሮ እንግዳ እሸቴ ለግንባታው የሚውሉ የጥሬ እቃ ጥራትን በሚመለከት አስፈላጊው ክትትል ማድረግ ተገቢ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

እርሳቸው ግድቡን በጎበኙበት ወቅት ለግንባታ የሚውሉ ብረቶች ለብልሽት ተዳርገው መታዘባቸውን አንስተው ጥንካሬና እድሜ የሌላቸው ብረቶች ለግብአት እንዳይውሉ ሲሉም ስጋታቸውን ገልፀዋል።

ከቅድስተ ማርያም ዩኒቨርሲቲ የተወከሉት አቶ አየለ ደሴ በበኩላቸው በግንባታው ላይ ያሉ መሃንዲሶችና ኢንጅነሮች ብቃት እንደገና ሊታይ ይገባል ሲሉ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።

ከባለሙያዎች ብቃት ማነስ ባሻገር የግብአት አቅርቦቱን መፈተሽ እንዲሁም በአማካሪነት የተሳተፉት አካላት ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ማድረግም ያስፈልጋል ብለዋል።

ከዲያስፖራ ማህበር ተሳታፊ የሆኑት ዶክተር ዮሃንስ ገብረስላሴ ደግሞ ዲያስፖራው ማህበረሰብ ሁለንተናዊ ተሳትፎውን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

የግድቡን የግንባታ ሂደት በሚመለከት ይስተዋል የነበረውን የመረጃ ክፍተት በማስተካከል ህዝቡ እውነተኛና ወቅታዊ መረጃ እንዲደርሰው ማድረግም ይገባል ብለዋል።

በመንግስት በኩል ቀደም ሲል ይህ ባለመሆኑና በተለይም የሚያጋጥሙ ችግሮችን ይፋ ባለማድረግ ዲያስፖራው በግድቡ ላይ ያለውን አመኔታ ሸርሽሮት ቆይቷል ብለዋል ዶክተር ዮሃንስ ።

የግድቡን ግንባታ በመቃወም ለፖለቲካ ፍጆታ የሚያውሉ አካላትን መንግስት በዝምታ መለፍ የለበትም ያሉት ደግሞ ከበጎ አድራጎት ድርጅት ማህበራት የተወከሉት አቶ ጅብሪል ማኬ ናቸው።

ከኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽን አቶ ጌታሁን ሁሴን ደግሞ በባለሃብቶችና በድርጅቶች ለግድቡ ግንባታ አስተዋፆ ለማድረግ የገቡትን ቃል መፈፀም አለባቸው ብለዋል።

በተገባው ቃል መሰረት በወቅቱ ተከታትሎ ገቢ መደረጉን የሚቆጣጠር አካል ባለመኖሩ በተለይ አንዳንድ ባለሃብቶች በአደባባይ ቃል ገብተው ሳይተገብሩ ለስምና ዝና ግብአት እያዋሉት መሆኑንም ጠቁመዋል።

"ለግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ በተለይ ወጣቶች በገንዘብ፣ እውቀቱና ጉልበት የማገልገል ፍላጎት ቢኖራቸውም የማስተባበሩ ሂደት በመቀዛቀዙ ተሳትፎው ቀንሷል" ያለው ደግሞ ከአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ወጣት ሚሊዮን ከበደ ነው።

በመሆኑም ፅህፈት ቤቱ በአዲስ መንፈስ ማህበረሰቡ በግድቡ ላይ ያለውን ግንዛቤ እንዲዳብር ማድረግና ተሳትፎውን እንዲያጠናክር መነቃቃት ይጠበቅበታል ብሏል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሃሮ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የግንባታ ግብአትን በሚመለከት ብረታብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፕሬሽን (ሜቴክ) ጥራቱን ያልጠበቀ ግብአት ያቀርብ ነበር ያሉት ስራ አስኪያጁ በአሁኑ ወቅት ስራውን በባለቤትነት የተረከበው ሳሊኒ ብልሽት ያጋጠማቸውን ቦታዎች በመለየት እየጠገነ ነው ብለዋል።

በቀጠይ ከግብአት አቅርቦት ጥራት ጋር ተያይዞ ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር ለማድረግ ከአቅራቢዎች ጋር በመነጋገር ጥራት ያለው እቃ እንዲቀርብ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

የሙያተኞችን፣ኢንጅነሮች፣ መሃንዲሶችና ድጋፍ ሰጪዎችን በሚመለከትም የፕሮጀክቱ አሰራር ሪፎርም ሲደረግ አብሮ እንዲሻሻል ተደርጓል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት 10 ነጥብ 4 ሚሊዬን ሜትር ኪዩብ ውሃ መሞላት ያለበት ማጠራቀሚያ ግድብ 80 በመቶ ተጠናቀቀ ሲሆን ኮርቻ ግድብም ከ93 በመቶ በላይ ተጠናቋል ነው ያሉት።

የግድቡን የጎርፍ ማስተንፈሻ በሚመለከትም 99 በመቶ ተጠናቋል ያሉት ስራ አስኪያጁ የሲቪል ስራዎቹ በታቀደላቸው ግዜ እየተከናወኑ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

ይሁን እንጂ የኤሌክትሮ መካኒካል ስራው በአሁኑ ወቅት 25 በመቶ ብቻ መከናወኑን እንዲሁም የብረታብረት ስራው 13 በመቶ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁን አጠቃላይ የግንባታው 65 በመቶ እንደደረሰና በታቀደለት ጊዜ ላለመጠናቀቁ የኤሌክትሮኒካልና ብረታብረት ስራው በመዘግየቱ እንደሆነም አስረድተዋል።

ግንባታውን በቀጣዮቹ አራት ዓመት ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅና በሙሉ አቅሙ ኃይል ማመንጨት እንዲችል የነበሩትን ችግሮች በመለየት ጠንካራ የፕሮጀክት አስተዳደር አሰራር በማሻሻል ወደ ስራ ተገብቷል።

የኮንትራክተሮች ምርጫ ላይ ጥንቃቄ በማድረግ ክትትል የሚደረግ እንደሆነና በአሁኑ ወቅት ስራ ላይ ያሉት ጂአልስቶም ቮይት አይድሮምና ሳሊኒ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዘርፉ እውቅና ያለቸው ቢሆኑም ወቅታዊ ክትትል በማድረግ ግንባታውን ለማፋጠን በትኩረት ይሰራልም ብለዋል።

ጽህፈት ቤቱም በአዲስ መልክ ወቅታዊ መረጃዎችን ለህዝብ በማድረስ እንዲሁም ግንባታውን የመጎብኘት ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይሰራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም