ህብረተሰቡን የበለጠ ተደራሽ ሊያደርግ የሚያስችል አሰራር ልተገብር ነው-ኢሳት - ኢዜአ አማርኛ
ህብረተሰቡን የበለጠ ተደራሽ ሊያደርግ የሚያስችል አሰራር ልተገብር ነው-ኢሳት
አዲስ አበባ ጥር 9/2011 የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን /ኢሳት/ ህብረተሰቡን የበለጠ ተደራሽ የሚያደርግ አሰራር ሊተገብር መሆኑን አስታወቀ።
ቴሌቭዥኑ ከተመሰረተ 8 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን ዜና፣ ውይይት፣ የመዝናኛና የስፖርት ፕሮግራሞችን ወደ ኢትዮጵያና ወደ ሌሎች የዓለም ክፍሎች በማሰራጨት ላይ የሚገኝ የሚዲያ ተቋም ነው።
ሚዲያው ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ለውጥ እንዲመጣ ሲታገል እንደነበርና በአገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ተከትሎ የተደረገን ጥሪ ተቀብሎ በኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ከፍቶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ በኢትዮጵያ የኢሳት ተጠሪ ኢንጅነር ሳባ አታሮ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ጠቅሰዋል።
ድርጅቱ ለበርካታ ዓመታት በተለይም በፖለቲካው ዘርፍ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ እንደቆየና አሁን ላይ በአገሪቱ በተፈጠረው የለውጥ ሂደት በመታገዝ ወደ አገር ቤት በመምጣት ስራውን እያከናወነ እንደሚገኝም ገልፀዋል።
ኢሳት በኢትዮጵያ የነበረውን ጭቆና በመታገል አሁን ለመጣው ለውጥ ትልቅ ድርሻ ማበርከቱን ገልፀው በቀጣይ ከፖለቲካው ባሻገር በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በስፋት በመስራት የተጀመረውን ልማት ለማስቀጠል እንደሚሰራም ተናግረዋል።
የካቲት ዘጠኝ በሚሊኒየም አዳራሽ አገር ውሰጥ ገብተው ስራ መጀመራቸውን ተከትሎ አጋራቸው ለሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ የምስጋና ፕሮግራም እንዲሁም ሚዲያውን ለማስቀጠል ህዝቡ ያለውን አጋርነት የሚያሳይበት መድረክ መዘጋጀቱንም ገልፀዋል።