ለጥምቀት በዓል በሰላም መከበር ህብረተሰቡ ትብብር እንዲያደርግ ተጠየቀ

61

አዲስ አበባ ጥር 9/2011 የከተራና የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር ኅብረተሰቡ ለጸጥታ አካላት ትብብር እንዲያደርግ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ።

ኮሚሽኑ በዓሉ በሰላም እንዲከበር አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁንም አስታውቋል።

የኮሚሽኑ የኢንዶክትሪኔሽንና ህዝብ ግንኙነት ምክትል ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ ለኢዜአ እንዳሉት ህብረተሰቡ ስጋት ውስጥ ሳይገባ በዓሉን በሰላም እንዲያከብር ኮሚሽኑ ከሌላው ጊዜ በተጠናከረ መልኩ ዝግጅት አድርጓል።

ጃን ሜዳና ሌሎች ታቦታት በሚያርፉባቸው የከተማዋ  ቦታዎች በዓሉን ለማክበር የሚሄደው ሰው ምንም ዓይነት የጸጥታ ችግር እንዳያጋጥመው ኮሚሽኑ አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቋል።

የጸጥታ ስራውን ከወጣቶች ጋር ለመስራት ዝግጅት ማድረጋቸውን በመግለጽ፤ ሌላው የህብረተሰብ ክፍልም ከፍተሻ ጀምሮ የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

በዓሉ ከኃይማኖታዊ ስርዓትና የእምነቱ ተከታዮች ከሚያሳዩት ባህል ተቃራኒ የሆነ እንቅስቃሴን ወደ በዓሉ ስፍራ ይዞ መሄድ የተከለከለ መሆኑንም አሳስበዋል።

በተጨማሪም ህጋዊ ፈቃድ ያላቸውን መሳሪያ ጨምሮ ስለታማ ነገሮችንና የጦር መሳሪያን ወደ በዓሉ ቦታ ይዞ መሄድ የተከለከለ መሆኑንም አሳስበዋል።

የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይኖርም በሁሉም ቦታዎች የትራፊክ ፖሊስ አባላት የሚሰሩ ሲሆን ሌሎች የፖሊስ አበላትም ከጥር 10 እስከ 13 ባሉት ቀናት ከቢሮ ስራ በተጨማሪ የጥበቃ ሽፋን እንዲሰጡ አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል።

የጥምቀትና ከተራ በዓል በርካታ ሰው የሚንቀሳቀስበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ  የኪስ ስርቆት፣ ሰዎችን ማታለል፣ በሽተኛ መስሎ መለመንና ሌሎች ወንጀሎችም ሊፈጸሙ እንደሚችሉም አስገንዝበዋል።

በመሆኑም ህብረተሰቡ ጥንቃቄ በማድረግ ከተለመደው ውጪ ለየት ያሉ እንቅስቃሴዎችን ሲያይ በአካባቢው ለሚገኙ የጸጥታ አባላት እንዲያሳውቁ ጠይቀዋል።

አሽከርካሪዎችና እግረኞችም ተገቢውን የትራፊክ ህግ በማክበር እንዲንቀሳቀሱም ኮማንደር ፋሲካ ጠይቀዋል።

በዓሉን ለመታደም ከውጭ አገራት የሚመጡ ጎብኚዎችም ደህንነታቸው ተጠብቆ ያለ ስጋት በዓሉን እንዲያከብሩ አስፈላጊውን ክትትል   እንደሚያደርጉና ህብረተሰቡብ የተለመደ የኢትዮጵያዊነት ባህሉን እንዲያሳይ ጠይቀዋል።

ከጸጥታ ጋር ተያያዥ የሆኑና አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙም ጥቆማ ለመስጠትና የፖሊስ አገልግሎት ለማግኘት በነጻ የስልክ መስመር 991 ወይም 011 1-11 01 11 ስልክ ቁጥር መጠቀም እንደሚቻል አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም