በኢትዮጵያ 88 በመቶ ህጸናት ድህነትና ዘርፈ ብዙ ችግሮች አሉባቸው-ጥናት - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ 88 በመቶ ህጸናት ድህነትና ዘርፈ ብዙ ችግሮች አሉባቸው-ጥናት
አዲስ አበባ ጥር 9/2011 በኢትዮጵያ እድሜያቸው ከ 18 ዓመት በታች የሆኑ 88 በመቶ ህጸናት የበዙ መሰረታዊ የማህበራዊ አገልግሎት ችግሮች እንዳሉባቸው ተገለጸ።
የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲና 'ዩኒሴፍ' በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የህጻናትን ዘርፍ ብዙ ችግሮችና የድህነት ምጣኔን የሚያሳይ ሪፖርት አቅርበዋል።
በዚህም በኢትዮጵያ ከ18 ዓመት በታች ካሉት 41 ሚሊዮን ህጻናት ውስጥ 36 ሚሊዮን ወይም 88 በመቶ የሚሆኑት ዘርፈ ብዙ የመሰረታዊ አገልግሎት ተደራሽነት ችግሮች እንዳሉባቸውና በድህነት ውስጥ እንደሚገኙ በሪፖርቱ ተገልጿል።
በዚህም ህጻናቱ በሶስት ጉዳዮች መሰረታዊ አገልግሎት ያልተሟላላቸው ናቸው ሲል ሪፖርቱ አሳይቷል።
ጥናቱ የህጻናቱን ዘርፈ ብዙ ችግሮችና የድህነት ምጣኔውን ለመለካት ዘጠኝ መስፈርቶችን ከግምት ያስገባ ሲሆን በዚህም የህጻናት ዕድገት በተለይ መቀንጨር፣ የተመጣጠነ አመጋገብ ፣ ጤና፣ ውሃ፣ ንጽህናና የመኖሪያ ሁኔታ መስፈርቶችን በማካተት የተካሄደ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ ከትምህርትና ከጤና ጋር ተያያዥነት ያላቸው ግንዛቤዎች፣ መረጃዎችና ተሳትፎ ተጠቃለዋል።
ከእነዚህ ዘጠኝ መስፈርቶች ውስጥ ህጻናቱ የመኖሪያ ቤትና የንጽህና አገልግሎትን በተመለከተ ከፍተኛ እጥረት እንዳለባቸው ጥናቱን ያቀረቡት በኔዘርላንድ አገር የኢኮኖሚ ምሁር የሆኑት ዶክተር ክሪስ ዴ ኔውበርግ ጠቅሰዋል።
በተለይ በገጠር ያሉ ህጻናት 94 በመቶ የድህነት ምጣኔ የታየባቸው ሲሆን በከተሞች ደግሞ የድህነት ምጣኔው 46 በመቶ ነው ብለዋል።
የህጻናት ድህነት ምጣኔው በአዲስ አበባ 18 በመቶ፣ በአፋር፣ አማራና ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል 91 በመቶ መሆኑ ተገልጿል።
በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች 90 በመቶ ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ 89 በመቶ፣ በጋምቤላ 81 በመቶ፣ በትግራይ 80 በመቶ፣ በሀረሪ 63 በመቶ እንዲሁም ድሬዳዋ 56 በመቶ ህጸናት የድህነት ምጣኔ እንዳለባቸው ተጠቅሷል።
በሪፖርቱ መሰረት በኦሮሚያ 16 ነጥብ 7 ሚሊዮን፣ በአማራ 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን እንዲሁም ደቡብ ክልል 8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ህፃናትን በመያዝ ከፍተኛ የድህነት ምጣኔ የሚታይባቸው ክልሎች ናቸው ተብሏል።
የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ እንዳሉት ከአጠቃላይ የድህነት ምጣኔው በተጨማሪ የህጻናትን የድህነት ምጣኔ ማወቅ ያሉትን ችግሮች በመለየት መንግስትና ሌሎች ከህጻናት ጋር የሚሰሩ ተቋማት እንዲሁም ምሁራን አፋጣኝ መፍትሄ እንዲያስቀምጡ ይረዳል ብለዋል።
ሪፖርቱ እ.ኤ.አ ከ2011 እስከ 2016 ያለውን የኢትዮጵያን ህዝብ ቁጥርና የጤና ሰርቬይን መሰረት አድርጎ የተከናወነ ሲሆን ይህም የህጻናትን የድህነት ምጣኔ በ32 የአፍሪካ አገራት ለማወቅ አገልግሎት ላይ የዋለ ነው።
በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የህጻናት አድን ድርጅት/ዩኒሴፍ ተወካይ ሚሲስ ጂሊያን ሜልሶፕ በኢትዮጵያ ህጻናት ከሌሎች የማህበረሰቡ ክፍል በተለየ ለድህነት የተጋለጡ ናቸው ብለዋል።
ለወደፊቱ የአገሪቷ የኢኮኖሚ ዕድገትና ማህበራዊ ልማት በህጻናት ላይ መዋዕለ ንዋዩን ማፍሰስ እንዳለበት በማከል።
ኢትዮጵያ ሪፖርቱ በአስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የህጻናትን የድህነት ምጣኔ ለመቀነስና ዘላቂ የልማት ግብ ለማሳካት እንዲሁም ድህነትን ለመቀነስ በህጻናት ላይ ኢንቨስት በማድረግ ምጣኔውን በየዓመቱ በአራት በመቶ መቀነስ እንዳለባትም መክረዋል።
የማህበራዊ ልማትን በማፋጠን ለህጻናት ከፍተኛ በጀት መመደብ እንደሚያስፈልግና የተለያዩ ማህበራዊ ዘርፎች ላይ ከሚሰሩ ተቋማት ጋር በትብብር በመስራት የህጻናትን ፍላጎት ማሟላት ያስፈልጋልም ብለዋል።