ቀጥታ፡

በወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአምስት ሺህ ሜትር ሴቶች አትሌት ግርማዊት አሸነፈች

አሰላ ግንቦት 18/2010 በኢትዮጵያ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአምስት ሺህ ሜትር ሴቶች ውድድር አትሌት ግርማዊት ገብረእግዚአብሔር አሸነፈች። በአሰላ አረንጓዴ ስታዲየም እየተካሄደ ያለው ሻምፒዮናው ዛሬ አራተኛ ቀኑን ይዟል። ዛሬ በተካሄደ የአምስት ሺህ ሜትር ሴቶች የፍጻሜ ውድድር አትሌት ግርማዊት ገብረእግዚአብሔር ከጉና ንግድ አሸናፊ ሆናለች። እንዲሁም እጅጋየሁ ታዬ ከኦሮሚያ ክልል ሁለተኛ ስትወጣ ጽጌ ኃይለስላሴ ደግሞ ከትራንስ ኢትዮጵያ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። የአምስት ሺህ ሜትር ሴቶች ውድድር በነሐሴ ወር 2010 ዓ.ም በፊንላንድ ቴምፕሬ በሚካሄደው የዓለም አቀፍ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከምትካፈልባቸው ርቀቶች ውስጥ አንዱ ነው። በሌላ በኩል በወንዶች ከፍታ ዝላይ የጋምቤላ ክልል ተወላጁ አትሌት ዳኜ ሌም አሸናፊ ሆኗል።። የመከላከያው ተወዳዳሪ አዲር ጉር በዚህ ውድድር አንደኛ ከወጣው ዳኜ ሌም ጋር በእኩል ከፍታ 1 ሜትር ከ98 ሴንቲ ሜትር ነበር መዝለል የቻለው። ይሁን እንጂ አግዳሚውን ዘንግ ሲዘሉ በሚኖራቸው ንክኪ ወይም አጣጣል በሚባለው ህግ ተሸንፎ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል። "በከፍታ ዝላይ ከእኔ የተሻሉ ዘላዮች ከመጡ ሙሉ ትኩረቴን ወደ ስሉዝ ዝላይ ይሆናል’" ሲል በውድድሩ ተሸናፊ የሆነው የመከላከያው የከፍታና የስሉዝ ተወዳዳሪ አዲር ጉር ገልጿል። የመከላከያ ስፖርት ክለብ ተወዳዳሪ የሆነው አዲር በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ጨምሮ በአገር ውስጥ በሚደረጉ ሌሎች ውድድሮች በስሉስ ዝላይና በከፍታ ዝላይ የበላይነትን ይዞ ቆይቷል። ባለፉት ሁለት ዓመታት በከፍታ ዝላይና ስሉስ ዝላይ በኢትዮጵያ ነግሶ የነበረው አዲር ጉር አሰላ እየተካሄደ ባለው ስድስተኛው የኢትዮጵያ  ወጣቶች አትሌቲከስ ሻምፒዮና ግን የከፍታ ዝላይ የነበረው የበላይነት የሚጋራው አትሌት ብቅ ብሏል። አዲር ጉርን ያሸነፈው የሲዳማ ቡናው አትሌት ዳኜ ሌም በውድድር ወቅት ለስፖርት ተመልካቾች በሚያሳየው የተለያዩ ምልክቶች ተመልካቹን ሲያዝናና ነበር። ተመልካቾችን ማዝናናት ብቻ ሳይሆን በመጨረሻው ውጤት ቀንቶት ላለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት በስሉስና በከፍታ ዝላይ ነግሶ የነበረውን አዲር ጉርን ማሸነፍ ችሏል። ውድድሩን ካሸነፈ በኋላ ዳኜ ከኢዜአ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ በውድድሩ ጥሩ ዝግጅት ባለማድረጉ አዲር ጉርን አሸንፈዋለሁ የሚል ግምት እንዳልነበረው ገልጿል። በተለያዩ ምክንያቶች ለዚህ ወድድር ጥሩ ዝግጅት ሳያደርግ  ማሸነፍ የቻለው የከፍታ ዘላዩ ዳኜ በቀጣይ  ጠንከራ ልምምድ በመስራት ጠንከራ ተፎካካሪ ለመሆን አቅዷል። ይሁን እንጂ እንደ አገር በከፍታ ዝላይ ብቻ ሳይሆን በርዝመት ዝላይና በስሉስ ዝላይም ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አሳስቧል። በውድድሩ የተሸነፈው አትሌት አዲር ጉር እንዳለው በከፍታ ዝላይ ተፎካካሪ ሲመጣ ለእሱ ብርታት እንደሚሆነው ነው የሚናገረው። "በከፍታ ዝላይ ከእኔ የተሻሉ አትሌቶች ከመጡ የከፍታ ዝላይን ለእነሱ በመተው ከዚህ በተሻለ በምወደው የስሉስ ዝላይ ላይ ሙሉ ትኩረቴን አድርጌ መስራት እፈልጋለሁ" ብሏል። በከፍታ ዝላይ ብቻ ሳይሆን በርዝመት ዝላይና በስሉዝ ዝላይ እንደ አገር በደንብ ስላልተሰራ ተፎካካሪዎችን ማግኘት እንዳልተቻለ ነው የሚናገረው አዲር ጉር። በተለይም ስልጠናውን በማዘመን ከአገር አልፎ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪዎች ማግኘት እንደሚቻል ነው እምነቱ። በስሉዝ ዝላይም በአገሪቱ የበላይነት ያለውና በኢትዮጵያ ክብረወሰኑም የተያዘው በአትሌት አዲር ጉር ሲሆን በአሰላ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው ስድስተኛው የኢትዮጵያ የወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮናም በስሉስ ዝላይ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ መሆኑ የሚታወስ ነው። በአሰላ አረንጓዴ ስታዴየም ሲካሄድ የሰነበተው ስድስተኛው የኢትዮጵያ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ነገ ፍጻሜውን የሚያገኝ ይሆናል። በውድድሩ ማጠቃለያ ዕለት ከሚደረጉ የፍጻሜ ውድድሮች መካከል የአምስት ሺህ ሜትር ወንዶች እንዲሁም በሁለቱም ጾታዎች የሚካሄዱት የ1 ሺህ 500 ሜትር እና የ3 ሺህ መሰናከል ውድድሮች ተጠባቂ ናቸው።   ---END---
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም