ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በዓለም አቦካዶ ገበያ በስፋት መሳተፍ እንድትችል ምርቱን ለማስፋፋት እየተሰራ ነው

አዳማ ጥር 9/2011 ኢትዮጵያ በፈጣን ሁኔታ እየጨመረ ባለው የዓለም አቦካዶ ገበያ በስፋት መሳተፍ እንድትችል በኦሮሚያ ክልል ምርቱን ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።

በኦሮሚያ ግብርና ቢሮ የፕላንና ፕሮግራም ኃላፊ አቶ ክፍሌ በቀለ እንደገለጹት የአቦካዶ ልማትን ለማስፋፋት ያለፉት 10 ዓመታት የዓለም ገበያ ፍላጎት የዳሰሰ ጥናት ተካሂዷል።

በጥናቱ መሰረት እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ2004 እስከ 2013 በነበረው ጊዜ ውስጥ የዓለም የአቦካዶ ፍላጎት በአማካይ በ337 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

በ10 ዓመታት ጊዜ ውስጥ በአውሮፓ 238 በመቶ፣ በአሜሪካ 445 በመቶ፣ በቻይና ደግሞ 180 በመቶ የፍላጎት መጨመር መታየቱንም አቶ ክፍሌ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አርሶአደሮች በአሁኑ ወቅት ከአንድ ሄክታር መሬት ቡና የሚያገኙት ምርት 127 ሺህ ብር መሆኑን ገልፀው አቦካዶው ለዓለም ገበያ በመላክ ከአንድ ሄክታር መሬት 2 ሚሊዮን ብር ማግኘት እንደሚቻል በጥናት መረጋገጡን አመልክተዋል።

" ኢትዮጵያ በዘርፉ ባለው ሰፊ የገበያ ፍላጎት ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ በጥረት ላይ ትገኛለች" ያሉት የፕሮግራም ኃላፊ የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ  ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ጋር በመተባበር በክልሉ በ53 ክላስተሮች የማምረት ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል።

አቦካዶ ማምረት የጀመሩ ዞኖች ጅማ፣ ምስራቅ ሸዋና ምስራቅ ወለጋ ዞኖች ሲሆኑ "በቅርቡ ልማቱ ወደ 7 ዞኖች ይስፋፋል" ብለዋል ።

በዓለም ገበያ ተፈላጊ የሆነውን "ሃስ" የተባለ የአቦካዶ ዝርያ በብዛት ለማስፋፋት በዓመት 200 ሺህ ችግኞች የሚያወጡ 21 ዘመናዊ የችግኝ ማፈያ ጣቢያዎች በግብርና ትራንስፎርሜሽን ድጋፍ እየተገነቡ ናቸው ተብሏል ።

ጅማን በአቦካዶ ምርት የልህቀት ማዕከል ለማድረግ ሁለት የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች ሥራ መጀመራቸውን ከአቶ ክፍሌ ገለጻ ለማወቅ ተችሏል ።

በክልሉ በየዓመቱ ከ3 እስከ 4ሺህ ሄክታር መሬት በአቦካዶ ተክል ለመሸፈን የታቀደ ሲሆን ከእስራኤል አገር የመጣው ዝርያ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚደርስና ለ40 ዓመታት ያለማቋረጥ ምርት የሚሰጥ ነው ተበሏል።

ከኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ ከኦሮሚያ ክልል 40 ኩንታል የአቦካዶ ምርት ለሙከራ ወደ ውጭ አገር ተልኮ አንዱን ኪሎ ግራም ከ7 እስከ 10 ዶላር ተሸጧል።

ምርቱ በብዛት እንዲቀርብላቸው የተለያዩ አገራት ቢጠይቁም ቀድሞ በስፋት ባለመሰራቱ ማቅረብ እንዳልተቻለ አቶ ክፍሌ ተናግረዋል ።

ስፔን፣ እስራኤል፣ ሜክሲኮና ቺሊ የመሳሰሉ ከፍተኛ የአቦካዶ አምራቾች ለዓለም ገበያ ምርቶቻቸውን የሚያቀርቡበት ወቅት የኢትዮጵያ የአቦካዶ ምርት ከሚደርስበት ወቅት ጋር የማይገናኝ መሆኑ ደግሞ ለገበያው መልካም አጋጣሚ መሆኑ ተመልክቷል።

በምስራቅ ወለጋ ዞን በዋዩ ቱቃ ወረዳ በማህበር ተደራጅተው በአቡካዶ ተክል ልማት ላይ የተሳተፉ  ወጣቶች ተጠቃሚ መሆናቸው ተናግረዋል ።

በወረዳው የቦነያ ሞሎ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ታከለ ይገዙ በሰጠው አስተያየት አንዳለው 20 ሆነው በማህበር በመደራጀት በአቦካዶ ልማት ሥራ ተሰማርተዋል ።

ቀደም ሲል 21 ሺህ የአቡካዶ ተክል አሳድገው ያዳቀሉትን 5 ሺህ 833 የአቡካዶ ተክል ለአካባቢው አርሶ አደር በ350 ሺህ ብር በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን አመልክቷል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም