ቀጥታ፡

እስራኤል ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ ትቀጥላለች - ፕሬዝዳንት ሪቭሊን

አዲስ አበባ ሚያዝያ 25/2010 እስራኤል ለኢትዮጵያ የልማት ስራዎች የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሬዩቪን ሪቭሊን ተናገሩ። በአዲስ አበባ የሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲ "አዎንታዊ ተጽእኖ" በሚል ሃሳብ ኢትዮጵያና እስራኤል ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከር በሚችሉበት ሁኔታ ያዘጋጀው የውይይት መድረክ ዛሬ ተካሂዷል። ፕሬዝዳንት ሪቭሊን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ኢትዮጵያና እስራኤል ረጅምና ታሪካዊ የወዳጅነትና የልማት ትብብር አላቸው። ይህን የትብብር ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ በማሸጋገር ረገድ የሁለቱ መንግስታት መሪዎች በተለያዩ ጊዜያት የትብብር ስምምነቶች በመፈራረም ወደ ተግባር መቀየሩን ገልጸዋል። እስራኤል በተራድኦ ድርጅቶቿ አማካኝነት በኢትዮጵያ ለሚከናወኑ የልማት ተግባራት ድጋፍ እያደረገች መሆኑን አውስተዋል። ይህንኑ ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥልና በተለይም ኢትዮጵያ የዘላቂ ልማት ግቦቿና ሌሎች የልማት እቅዶቿ ውጤታማ እንዲሆኑ የምታደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ ተናግረዋል። እስራኤል ላለፉት 70 ዓመታት በውሃ ልማት፣ በጤና፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በመሰረተ ልማት፣ በሳይበር ደህንነት፣ በኢነርጂና በኢኮኖሚ ልማት ውጤታማ ስራዎችን መስራቷ ገልጸዋል። በዘርፎቹ ያላትን ልምድ ለኢትዮጵያና ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ለማካፈል ፍላጎት እንዳላትም ጠቁመዋል። እስራኤልና አፍሪካ በተለያዩ መስኮች ያላቸው ትብብር መጠናከር በቀጣይ የተሻለና ብሩህ ዓለም ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል። የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም በበኩላቸው የውይይት መድረኩ አገራቱ ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ከእስራኤል በኢነርጂ፣ በውሃ ልማትና በትምህርት ተሞክሮ መቅሰም እንደምትፈልግ ጠቅሰዋል። የእስራኤል አምራቾች ማህበር ፕሬዝዳንት ሚስተር ሽራጋ ብሮሽ የአገራቸው ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ከሚገኙ አምራቾች ጋር በትብብር መስራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። የኩባንያዎቹ በትብብር መስራት የአገራቱን የንግድ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚያግዝም ተናግረዋል። በውይይት መድረኩ እስራኤልና ኢትዮጵያ በጤና፣ በህዋ ሳይንስ ቴክኖሎጂ፣ በመልክዓ ምድራዊ የቁጥር ትንተና፣ በውሃ ኃይል ማመንጫና በታዳሽ ኃይል ዘርፎች በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል። ስምምነቶቹን በዘርፉ የሚገኙ የአገራቱ የመንግስት ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ተፈራርመዋል። በኢነርጂ፣ በመሰረተ ልማት፣ በውሃ ልማት፣ በትምህርት፣ በግብርና፣ በጤናና የጤና ሳይንስ ዘርፍ፣ የምግብ ዋስትና፣ የማህበረሰብ ልማትና ሰብአዊ እርዳታ የሚሰሩ የሁለቱ አገራት ተቋማት ግንኙነታቸውን ማጠናከር በሚችሉበት ሁኔታ ላይም ውይይት አድርገዋል። ኢትዮጵያና እስራኤል ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1956 ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም