በሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ የሚታዩ ተግዳሮቶችን በመፍታት በፈጠራ የተካነ የሰው ኃይል ማፍራት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ የሚታዩ ተግዳሮቶችን በመፍታት በፈጠራ የተካነ የሰው ኃይል ማፍራት ይገባል
ጎባ ግንቦት 18/2010 በሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በጥናትና ምርምር በመፍታት ብቁና በፈጠራ ክህሎት የተካነ የሰው ኃይል ማፍራት እንደሚገባ የዩኒቨርሲቲ ሙሁራንና የሥራ ፈጠራ ባለሙያዎች ገለጹ ፡፡ " አዳዲስ ፈጠራዎች ለውጤታማ የንግድ ሥራና ቀጣይነት ላለው ልማት!" በሚል መሪ ሀሳብ ሁለተኛው አገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ጉባኤ በመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ከትናንት ጀምሮ በባሌ ጎባ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡ በጉባኤው ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ጂኒያስ የሥራ ፈጠራ ጥበብ ማሰልጠኛና የቢዝነስ ምክር አገልግሎት ማዕከል መስራችና ኢንተርፕርነር ዶክተር ወሮታው በዛብህ እንደተናገሩት ድህነትም ሆነ ባለፀጋነት ምርጫዎች ናቸው። ሁሉም ሰው የፈጠራቸውና የኖረባቸው የአስተሳሰብ ውጤቶች መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ "ለስራ ፈጠራ ጥበብ ዋናው ነገር በጎ አመለካከትን ማዳበር ነው" ያሉት ዶክተር ወሮታው፣ ይህንን እሳቤ በመያዝ ከዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ተነስቶ ስኬታማ ደረጃ ላይ መድረስ እንደሚቻል ከሕይወት ተሞክሯቸው በመነሳት ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡ ዶክተር ወሮታው በሀገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ብዙ ጥናትና ምርምሮች እንደሚካሄዱ ጠቁመው የምርምር ወጤቶቹ የማህበረሰቡን ችግር በመፍታትም ሆነ ለፖሊሲ ግብዓት በመዋል በኩል ክፍተቶች እንዳሉ አመልክቷል፡፡ በመሆኑም ሙሁራን ከምርምር ሥራ ባለፈ ሥራ ወዳድና ለሀገር ኢኮኖሚ የበኩሉን አስተዋጽኦ የሚያበረክት ዜጋ ለማፍራት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡ ወጣቶችም መንግስት በዘርፉ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ የሚያደርገውን ጥረት እንደ መነሻ በመጠቀም አወንታዊ አመለካከት በማዳበር ወደ ስኬታማነት ጫፍ መድረስ እንደሚችሉ መክረዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን እንቅስቃሴ አስመልክቶ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ አቶ ዳንኤል ፈየራ በበኩላቸው መንግስት በሀገሪቱ የሚታየውን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይሁንና በክልሉ የሚገኙ ሁሉንም የሥራ አማራጮች በመለየት ወደ ሥራ ለገቡ ወጣቶች የሚደረግ ድጋፍና ክትትል ላይ ውስንነቶች እንዳሉ በጥናታቸው መለየታቸውን ተናግረዋል፡፡ " በዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ሙሁራንና ዘርፉን የሚመሩ በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት ሴክተር መስሪያቤቶች በቅንጅት ሊሰሩ ይግባል" ብለዋል፡፡ በሥራ ፈጠራ ዘርፈ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በጥናት በመለየት ሀገሪቱ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር የምታደርገውን ሽግግር ለማፋጠን በትኩረት መስራት እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ አብዱልናስር አብዱልመልክ ናቸው ፡፡ የዩኒቨርሲቲው የምርምር ማህበረሰብ አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ስሜነህ ቤሴ በበኩላቸው ተቋሙ በሥራ ፈጠራ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በጥናትና ምርምር ከመለየት በሻገር የዘርፉን አቅም ለማጎልበት የሚያስችል ሥራ እየሰራ ነው ፡፡ ዩኒቨርሲቲው በተያዘው ዓመት የጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት አቅምን ለማሳደግና የሥራ ፈጠራን ለማጎልበት የሚያስችል "የስራ ፈጠራ ማእከል" አቋቁሞ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ ወደ ሥራ መግባቱን በማሳየነት አንስተዋል፡፡ ማዕከሉ ከዩኒቨርሲቲ ለሚመረቁ ተማሪዎች፣ በአካባቢው ሥራ አጥ ለሆኑ ወጣቶችና ዘርፉን ለሚመሩ የመንግስት ሴክተር መስሪያቤቶች በስራ እድል ፈጠራ አጫጭር ስልጠናዎችን በመስጠት በዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረውም አመልክቷል፡፡ ከተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ሙሁራንና ኢንተርፕረነሮች የተሳተፉበትና ለሁለት ቀናት የሚቆየው አገር አቀፍ ኮንፈረንስ በሥራዕድል ፈጠራና ተያያዝ በሆኑ መስኮች የተለያዩ ጥናቶች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል፡፡ የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ከ390 በላይ ምርምሮችና የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክቶችን ማካሄዱን ከዩኒቨርሲቲው የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡