ቀጥታ፡

'በኦነግ ሸኔ ላይ በአየር ኃይል የታገዘ ጥቃት ተፈጽሟል' ተብሎ የሚናፈሰው ወሬ ሐሰተኛ ነው - የአየር ኃይል ዋና አዛዥ

አዲስ አበባ ጥር 8/2011 'በምዕራብ ኦሮሚያ በኦነግ ሸኔ ላይ በአየር ኃይል የታገዘ ጥቃት ተፈጽሟል' ተብሎ በማህበራዊ ድረ-ገጾች የሚናፈሰው ወሬ ሃሰተኛ መሆኑን የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ይልማ መርደሳ ገለጹ።

ብርጋዴር ጄኔራሉ በምዕራብ ኦሮሚያ የጸጥታ ችግር መኖሩንና መንግስት ብዙ ትዕግስት ማሳየቱን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።

መንግስት የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ እርምጃ መውሰድ የጀመረ ቢሆንም በማህበራዊ ድረ-ገጾች 'በአየር ኃይል የታገዘ ጥቃት ተፈጽሟል' ተብሎ የሚነዛው ወሬ ሃሰተኛ መሆኑን አስታውቀዋል።

በአካባቢው ከምድር ውጊያና የሰፈር ግጭት ያለፈና አውሮፕላን መጠቀም የሚያስገድድ ሁኔታ አለመኖሩንም ነው የገለጹት።

የሚናፈሰው ሀሰተኛ ወሬ ሆን ተብሎ የሠራዊቱንና የተቋሙን ስም ለማጉደፍ የሚካሄድ ዘመቻ እንደሆነም በአጽንኦት ተናግረዋል።

በማህበራዊ ድረ-ገጾቹ የአየር ኃይል አውሮፕላን ተመቶ ወድቋል የተባለውም ከእውነት የራቀ መረጃ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ህብረተሰቡ በአገሪቱ ሠላም እንዳይኖርና በዚህም ቀውስ ለመጠቀም የሚሹ ኃይሎች መኖራቸውን 'ሊገነዘብ ይገባል' ያሉት ብርጋዴር ጄኔራል ይልማ ከመሰል ሀሰተኛ መረጃዎች ራሱን እንዲያርቅ አሳስበዋል።

የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃንም በሀሰተኛ መረጃ አገር እንዳይበጠበጥ በኃላፊነት ስሜት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም