ቀጥታ፡

ባህል ከማንነት መገለጫ ባለፈ ለቱሪዝም ልማት እንዲውል እየተሰራ ነው - የኢትዮጵያ ብሄራዊ የባህል ማዕከል

አክሱም ግንቦት18/2010 ባህል ከማንነት መገጫ ባለፈ ለቱሪዝም ልማት ለማዋል ለሚደረገው ጥረት ስኬታማነት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የባህል ማእከል አስታወቀ፡፡ “ባህል ለሰላም፣ ልማት እና ሀገራዊ አንድነት'' በሚል መሪ ቃል ክልል አቀፍ የባህል ሳምንት  በአክሱም ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡ የማእከሉ ዋና ዳሬክተር  ዶክተር እልፍነሽ ሃይሌ  በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ባህል ከማንነት መገለጫ ባለፈ ለሀገር ሰላምና እድገት ከፍተኛ  ፋይዳ አለው፡፡ የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባህላዊ እሴቶችና መገለጫዎችን ለቱሪዝም ልማት ለማዋልና ለትውልድ ለማስተላለፍ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ “የባህል ሳምንት መከበሩም ህዝቦች ለዘመናት ያቆዩትን የአብሮነት፣ የመቻቻልና የመፈቃቀር ባህል ይበልጥ እንዲጎለብትና ለትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ ያስችላል'' ብለዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም በዘርፉ ጥናትና ምርምር  ለሚያካሄዱ ግለሰቦች እና ተቋማት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልፀዋል፡፡ በመሆኑም  በባህሉ የሚኮራ ትውልድ ለመፍጠርና ዘርፉን ለቱሪዝም ልማት ለማዋል ለሚደረገው ጥረት ስኬታማነት በየደረጃው ያለው አካል በኃላፊነት  ሊሰራበት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ የትግራይ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ሃይሉ በበኩላቸው በክልሉ የባህልና ኪነ ጥበብ ፌስቲቫል መዘጋጀቱ የማንነት መገለጫ የሆኑ  እሴቶችን በመጠበቅና በማስተዋወቅ ለትውልድ እንዲተላለፍ የሚደረገውን ጥረት ያግዛል፡፡ እንዲሁም በየአከባቢው የተጠናከረ የባህል ቡድን ለመፍጠር  እንደሚያስችል ገልፀዋል፡፡ በዝግጅቱ 54ቱ ወረዳዎች በመሳተፍ ላይ ሲሆኑ የባህል ውድድር፣ የጎዳና ትእይንትና የባህል ኤግዚቪሽን በማካሄድ ላይ ናቸው፡፡ ትናንት የተጀመረውንና ለአምስት ቀናት የሚቆየውን የባህል ሳምንት ያዘጋጁት የኢትየጵያ ብሄራዊ የባህል ማእከልና የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም በመተባበር ነው፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም