በኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ሙገር ሲሚንቶና ጣና ባህርዳር አሸነፉ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ሙገር ሲሚንቶና ጣና ባህርዳር አሸነፉ
አዲስ አበባ ግንቦት 18/2010 በ2010 የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም በተደረጉ ጨዋታዎች ሙገር ሲሚንቶና ጣና ባህርዳር አሸነፉ። ሙገር ሲሚንቶ መከላከያን በሶስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሶስት ለዜሮ በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ ጣና ባህርዳር አዲስ አበባ ፖሊስን በአራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሶስት ለአንድ መርታት ችሏል። የፕሪሚየር ሊጉ መርሃ-ግብር ነገም ሲቀጥል በክልል ከተማ ሮቤ ላይ መዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከፌዴራል ማረሚያ ከጠዋቱ 2 ከ30 ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ የሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ መርሃ-ግብር ሁለት ጨዋታዎች ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም የሚካሄዱም ይሆናል። በዚሁ መሰረት የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ከጌታዘሩ ስፖርት ክለብ ከጠዋቱ 2 ከ30 የሚካሄድ ሲሆን ፌዴራል ማረሚያ ከኢትዮጵያ ውሃ ስራዎች ከረፋዱ 4 ከ30 ላይ ይጫወታሉ። የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ በሁለቱም ጾታዎች ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል። በሌላ በኩል በ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ የሴቶች ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ-ግብር ዛሬ ባህርዳር በተደረገ ጨዋታ አማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይን ወልቂጤ ከተማን 66 ለ48 በሆነ ውጤት አሸንፏል።