በጋምቤላ ከተማ ህገ -ወጥ የጦር መሳሪያና የገንዘብ ኖቶች ተያዙ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ከተማ ህገ -ወጥ የጦር መሳሪያና የገንዘብ ኖቶች ተያዙ
ጋምቤላ ጥር 7/2011 በጋምቤላ ከተማ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያና ከ328 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥና የውጪ ገንዘብ ኖቶች ከነተጠርጣሪዎቹ ጋር መያዙን ፖሊስ አስታወቀ፡፡
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳይመን ቲያች ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት የተያዙት የገንዘበ ኖቶች 125 ሺህ 850 የኢትዮጵያ ብር እና 202 ሺህ 700 ደግሞ የደቡብ ሱዳን ፎን የሚባል ነው፡፡
እንዲሁም ህገ ወጥ የሆነ አንድ ሽጉጥ ከ20 ጥይቶች ጋር ተይዟል፡፡
ፖሊስ የገንዘብና የጦር መሳሪያውን ሊይዝ የቻለው አንድ የባጃጁ አሽከርካሪን በመጠርጠር ድንገተኛ ፍተሻ ሲያደርግ ተደርሶበት እንደሆነ ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡
በዚህም በባጃጁ ውስጥ የብር ኖቶቹ ማገኘታቸውን ተከትሎ አሸከርካሪው የእሱ እንዳልሆነና ሁለት ግለሰቦች ሌላ ቦታ እንዲያደርስላቸው ጠይቀውት እንደሆነ መግለጹን አመልክተዋል፡፡
አሽከርካሪው መርቶ በማሳየትም ግለሰቦቹ ሲያዙ የጦር መሳሪያው ከነጥይቱ እንዲሁም ገንዝብ ጭምር እንደተገኘባቸው ገልጸዋል፡፡
በተባባሪነት የባጃጁ አሽከርካሪውን ጨምሮ ሶስቱም ግለሰቦች በተጠርጣሪነት ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑንና እንደተጠናቀቀም ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት እንደሚላክ አስታውቀዋል።
ክልሉ በተለይም ከደቡብ ሱዳን ጋር ሰፊ የድንብር ወሰን ከመኖሩ ጋር ተያይዞ ህገ- ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውሩ እየተበራከተ በመሆኑ ችግሩን ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልል ባለፈው ሳምንት 27 የክላሽና የብሬን ጦር መሳሪያዎች ጨምሮ ሌሎችም ህገ ወጥ የጦር መሳሪዎችና ጥይቶች መያዛቸውን ኢዜአ በወቅቱ ዘግቧል፡፡