ቀጥታ፡

የሊግ ካምፓኒ ምስረታ አስመልክቶ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያዘጋጀው ውይይት ዛሬ ተካሂዷል

አዲስ አበባ ጥር 7/2011 ክለቦች ራሳቸው ባቋቋሙት የሊግ አስተዳደር የፕሪሚየር ሊጉን ውድድር መምራት የሚያስችላቸውን የሊግ ካምፓኒ ምስረታ አስመልክቶ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያዘጋጀው ውይይት ዛሬ ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የሊጉን ውድድር በራሳቸው መምራት ጉዳይ ከ1990 ዓ.ም ፕሪሚየር ሊጉ መካሄድ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሲነሳ የነበረ ጉዳይ ነው።

ክለቦች ባላቸው የሀሳብ ልዩነትና አለመግባባት ምክንያት የክለቦች ሊግ በተለያየ ጊዜ ይቋቋማል ቢባልም እስካሁን ሀሳቡ ሀሳብ ብቻ ሆኖ ቀርቷል።

በግንቦት ወር 2010 ዓ.ም በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ በተካሄደው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ ወደስልጣን የመጣው የእግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራር ክለቦች የሊጉን ውድድር በራሳቸው ባቋቋሙት የሊግ ካምፓኒ እንዲያካሂዱ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ ይገኛል።

በመስከረም ወር 2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሊግ ካምፓኒውን ጉዳይ እንዲከታተሉና እንዲያስፈጽሙ አቶ አስጨናቂ ለማ፣ አቶ ሸረፋ ዴሌቾና አቶ ሰላሙ በቀለን መምረጡ የሚታወስ ሲሆን ጉዳዩን የሚመራ ኮሚቴም አቋቁሞ እየሰራ ነው።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ፌዴሬሽኑ ክለቦች ውድድራቸውን በራሳቸው እንዲመሩና እንዲያስተዳድሩ ቁርጠኛ አቋም መያዙን አስታውቀዋል።

ለዚህም ከክለቦች ጋር በተደረገ ውይይት ከስምምነት ላይ ተደርሶ ራሳቸው ክለቦቹ በ2011 ዓ.ም እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ውድድሩን ከመራው በኋላ ክለቦች ተሞክሯቸውን ወስደው ራሳቸው የሚያመሩበትን ሊግ ማቋቋም እንደሚችሉ መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።

በዚሁ መሰረት ክለቦች በ2012 የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ራሳቸው የሊጉን ውድድር እንዲመሩ እቅድ መያዙንና ለዚህም የሚያግዘው የሊግ ካምፓኒ ምስረታ ውይይት መዘጋጀቱን አመልክተዋል።

ለሊግ ካምፓኒው ምስረታ የሚረዳ ጥናት ላለፉት አራት ወራት ስምንት አባላት ባሉት የጥናት ቡድን ተካሂዶ መጠናቀቁንም ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ክለብ የህዝብ አስተዳደርና የልማት ማኔጅመንት ሃላፊ አቶ ገዛሀኝ ወልዴ የጥናቱን ጥቅል ሀሳብ ለክለቦቹና ለእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ አቅርበዋል።

በዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ደረጃ የክለቦች ሊግ አወቃቃር ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ስር ሆነው ክለቦች በራሳቸው የሊግ አስተዳደሩን የሚመሩበትና ሌላኛው ክለቦቹ ከፌዴሬሽኑ ተነጥለው ኩባንያ በመመስረት ውድድሩን የሚመሩበት የውድድር ፎርማት እንደሆነ አንስተዋል።

ክለቦቹ ከፌዴሬሽኑ ተነጥለው ኩባንያ የሚመሰርቱበት የሊግ አስተዳደር ክለቦች ከስፖንሰርና ከቴሌቪዥን መብት የተሻለ ገቢ ሊያገኙበት የሚችሉበት አስተዳደር እንደሆነ ነው ያመለከቱት።

በዓለም ላይ ያሉት አብዛኞቹ ፕሮፌሽናል ሊጎች በነዚህ በሁለቱ የሊግ አስተዳደር መዋቅሮች ሊጎቻቸውን እንደሚመሩና ፌዴሬሽኖችም ውድድሩን የማስተባበርና የመቆጣጠር ሃላፊነት እንዳላቸውም ነው አቶ ገዛሀኝ ያስረዱት።

የሊግ መዋቅሩ ክለቦች ህጋዊ ቁመና እንዲኖራቸው፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ያለው ጣልቃ ገብነትና ገንዘብ ተኮር ግንኙነቶች ስርአት ያለውና ጤናማ እንዲሆን ያስችላል። 

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ለግ በፌዴሬሽኑ ስር ሆኖ ክለቦች በራሳቸው አስተዳደር ቢመሩት የተሻለ እንደሚሆን ምክረ ሀሳባቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ "እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በውድድር ላይ ተጠምዶ ሌሎች ስራዎችን ማከናውን እየቻለ አይደለም የልማት ስራዎችን እያከናወነ አይደለም ትኩረቱን ወደ ልማቱ በማዞር ለመስራት እቅድ መያዙንና ክለቦች ደግሞ ሊጉን ተረክበው ውድድር እንዲያካሂዱ ጽኑ አቋም አለው" ብለዋል።

ለዚህም ፌዴሬሽኑ ለላፉት ሰባት ወራት የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል ያሉት ፕሬዚዳንቱ ክለቦች ውድድሩን መምራተቸው ከገቢና አጠቃላይ አቅማቸውን ከማጠናከር አንጻር አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል።

ፌዴሬሽኑ ለክለቦች ጽህፈት ቤት በመስጠትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ እስከ መጨረሻው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

በቀጣይም በክለቦቹ የሚቋቋመው ኮሚቴ በቀረበው ጥናት ላይ ተጨማሪ ሀሳቦችን መስጠት እንደሚችልና ቀጣይ በሚሰሩ ስራዎች ላይ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥም ነው አቶ ኢሳያስ ያስረዱት።

ተከታታይ ውይይቶችን ማድረግ፣ለሊግ ካምፓኒው የሚሆን ደንብና መመሪያ ማዘጋጀት፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ ማቋቋም፣ ፕሮፌሽናል ቀጠናዎችን መለየት ተግባር እንደሚከናወን አስረድተዋል።

ክለቦችም እስከ ጥር 14 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ለሚቋቋመው ኮሚቴ ተወካዮቻውን እንዲልኩም ተናግረዋል።

በአጠቃላይ ለሊግ ካምፓኒው ምስረታ ክለቦች ያላቸው አቋም መልካም እንደሚባልና ከድሮ አሰራር ወጥተን ወደ ፕሮፌሽናል ስርአት ለመምጣት ሁሉም ባለድርሻ አካል በቅንጅት መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም