ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ መጓተት ትልቁን ድርሻ መንግስት ይወስዳል-ኢንጂነር ታከለ ኡማ - ኢዜአ አማርኛ
ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ መጓተት ትልቁን ድርሻ መንግስት ይወስዳል-ኢንጂነር ታከለ ኡማ
አዲስ አበባ ጥር 7/2011 ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ መጓተት ትልቁን ድርሻ መንግስት ይወስዳል ሲሉ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ተናገሩ።
ዘንድሮ 134 ሺህ ተመዝጋቢዎችን የቤት ባለቤት ለማድረግ የተያዘው እቅድ በመንግስትና በተቋራጩ በኩል ያለው ችግር በፍጥነት ተፈቶ ዜጎች ተጠቃሚ መሆን እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
ከተማ አስተዳደሩ የ6 ወራት የአፈጻጸም አጭር ሪፖርት አቅርቦ በተቋራጮቹና በአማካሪዎች ላይ በሚስተዋሉ ችግሮች ላይ መክሯል።
በቀረበው ሪፖርትም የ20/80ም ይሁን የ40/60 ቤቶች ሊጠናቀቁ ከታሰበላቸው ጊዜ ከማለፋቸው በላይ አንዳንዶቹ የ5 እና የ6 ዓመታት ጊዜ ወስደውም መጠናቀቅ አልቻሉም ተብሏል።
ከዚህ ውስጥ ከ132 ሺህ ቤቶች በላይ ተጓተዋል፤ ከዚህም ሌላ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የኪራይ ቤቶች ግንባታ ከኋላው ተነስቶ ቀድሟልም ተብሏል።
ለዚህም እንደምክንያት የተነሳው በአማካሪዎች በኩል ተገቢውን ሙያና ክህሎት የያዘ ባለሙያን አለማሰማራትና የግንባታ አፈፃፀማቸው ዝቅተኛ በሆኑ ተቋራጮች ላይ የእርምት እርምጃ አለመውሰድ ነው።
በሌላ በኩል ተቋራጮች የፕሮጀክት አቅርቦትና የፋይናንስ አቅም ውስንነት መኖር፣ በኃላፊነት ስሜት አለመስራት ችግርም እንደነበረ ተገልጿል።
ተቋራጮች በበኩላቸው ሪፖርቱ የመንግስትን ትልቅ ክፍተት ያላየ መሆኑን ገልፀው እንዳውም ለቤቶች ግንባታ ውድቀት ትልቁ ድርሻ የመንግስት መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ስራ ተቋራጮች ማህበር ፕሬዝዳንት ኢንጂነር አመሃ ስሜ እንዳሉት ግብዓት ሳያቀርብ እንደሚቆይና ቢያቀርብም ለሚፈልጋቸው ተቋራጮች ብቻ የማቅረብ ስራ ይሰራ እንደነበር ተናግረዋል።
ውል በተገባው መሰረት እንዳይፈፀም የብረት፣ የሲሚንቶ፣ የፕሪካስትና ብሎኬት አቅርቦት በሌለበት ቤቶቹን በፍጥነት መገንባት እንደማይችሉም ተናግረዋል።
በተጨማሪም የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ሳይንሳዊ አሰራርን ተጠቀሙ ይላል እንጂ ራሱ እንደማይጠቀምና መጠቀምም እንደማይፈልግ አስታውቀዋል።
የዲዛይን ችግርም ሌላው ተቋራጮቹ በመንግስት በኩል ያነሱት ችግር ነው።
ከዚህ ውጪ ቤቶቹን ቶሎ ጨርሶ ለሚፈልገው ህብረተሰብ ማስተላለፍ የተቋራጩንም ወጪ የሚቀንስ በመሆኑ ፍላጎት እንዳላቸው ጠቁመው በመንግስት አካላት በኩል ግን ከመራዘሙ የሚጠቀሙት ነገር በመኖሩ ይህም ለመጓተቱ ምክንያት ነው ብለዋል።
ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ በመጨረሻ በሰጡት ምላሽ ለቤቶች ፕሮጀክት መጓተት ተቋራጩን ለመውቀስ አቅም እንደማይኖር በመናገር ትልቁን ድርሻ መንግስት ይወስዳል ብለዋል።
የተባሉ የአቅርቦትና የአሰራር ችግሮችን ለመፍታትም መንግስት አደረጃጀቱን በባለሙያ የማስተካከል ስራ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
የፋይናንስ ፍሰትን ለማስተካከልም ከብሄራዊ ባንክ ጋር ምክክር መደረጉን ገልፀዋል።
ከዚህ በመነሳትም በመንግስት በኩል የታየውን ክፍተት መንግስት ሲሞላ ተቋራጩ ደግሞ በራሱ በኩል ያለበትን ክፍተት በመፍታት የተጓተቱ ስራዎች ቶሎ መጠናቀቅ አለባቸው ብለዋል።
በተስፋ የሚጠብቀውን ህዝብ ባለቤት ለማድረግ በዚህ ዓመት ሊተላለፉ የታቀዱ 134 ሺህ ቤቶች ላይ ርብርብ እንዲደረግም ጠይቀዋል።
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዘሪሁን አምደማርያም በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ ችግር የነበረበት መሆኑን ገልፀው ችግሮቹን ለመለየትና ወደፊት ለመሄድ ምክክሩ አስፈልጓል ብለዋል።
ከውይይቱ በመነሳትም በያንዳንዱ ህንፃ ላይ የአፈፃፀም ግምገማ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
በዚህ ዓመት እስከሚቻለው ድረስ በማጠናቀቅ ቤቱን ባለበት ሁኔታ ለባለእድለኛው በማስተላለፍ እድለኛው እየተከታተለ እንዲጠናቀቁ እንደሚደረግ ይሆናል ነው ያሉት።
ከ134 ሺህ ውጪ ያሉትን ከ600 ሺህ በላይ የሚሆኑ ተመዝጋቢዎች ደግሞ በመንግስትና የግል አጋርነት፣ በማህበርና በበጎ አድራጎት ድርጅቶችም አማካኝነት በግንባታው የሚሳተፉበት ፕሮግራም መታሰቡን ጠቅሰዋል።
ለዚህም መንግስት ቦታ የማፈላለግና የዝግጅት ስራ የጀመረ ሲሆን የተገኙ ቦታዎችም መኖራቸውን አስታውቀዋል።