ከተሞቹ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ተባብረው ለመሥራት ስምምነት ደረሱ - ኢዜአ አማርኛ
ከተሞቹ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ተባብረው ለመሥራት ስምምነት ደረሱ
ባህርዳር ጥር 7/2011 ባህር ዳርና የአሜሪካዋ ማዲሰን ከተሞች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ተደጋግፎ ለመሥራት የእህትማማችነት ስምምነት ተፈራረሙ።
ስምምነቱን ያደረጉት የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙሉ ቀን አየሁና በማዲሰን ከተማ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ተወካይ ረዳት ፕሮፌሰር ራሄል ደሳለኝ ናቸው።
አቶ ሙሉቀን በዚሁ ወቅት ከተማዋ ከማዲሰን ከተማ ልምዶችን ለመቅሰም የሚያስችላት ስምምነት መደረጉ ፋይዳው ጉልህ መሆኑን ተናግረዋል።
ከተማዋ በዓለም ላይ ለመኖር ምቹ ከሚባሉ ከተሞች አንዷ ሆና ከሁለት ዓመታት በፊት መመረጧን አውስተው፣ከማዲሰን ጋር ያደረገችው ስምምነት ዓለም አቀፍ ተቀባይነቷን በማሳደግ ዘመናዊ ከተማነትን በተለይም የቱሪዝም አሰራር ሥርዓትን ለመዘርጋት ያግዛታል ብለዋል።
ረዳት ፕርፌሰር ራሄል በበኩላቸው የማዲሰን ከተማ አስተዳደር ከከተማዋ ጋር ያደረገውን ስምምነት ከአንድ ወር በፊት ማጽደቁን አስታውቀዋል። በዚህም10ኛዋ እህት ከተማ ሆና መመዝገቧን ተናግረዋል።
ባህር ዳር ከከተማዋ የእድገት ተሞክሮ የምትቀስምበት ዕድል እንደሚመቻችም ገልጸዋል።
ከተሞቹ ተመሳሳይ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ እንዳላቸው ያወሱት ረዳት ፕሮፌሰር ራሄል፣በሃይቅ የተከበበችውና የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓቷ ብክለት የማያስከትሉበትን ልምድ ለመካፈል ዝግጁ እንደሆነች አስታውቀዋል።
ከተሞቹ በሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ተባብረው እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የሁለቱ ከተሞች ተወካዮች እንግዶች ተገኝተዋል።