የፍትህ ተቋማት ለሰብዓዊ መብት መከበር የሚጫወቱትን ሚና ማሳደግ እንደሚገባ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
የፍትህ ተቋማት ለሰብዓዊ መብት መከበር የሚጫወቱትን ሚና ማሳደግ እንደሚገባ ተጠቆመ
አዲስ አበባ ግንቦት 18/2010 በኢትዮጵያ የፍትህ ተቋማት ለሰብዓዊ መብት መከበር የሚጫወቱትን ሚና ማሳደግ እንደሚገባ ተጠቆመ። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ስለ ሰብዓዊ መብት ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለማስረጽ የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ገልጿል። ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን ተቀብላ ማጽደቋ የሚታወቅ ነው። አቶ ግደይ ደገፉ በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ መምህር ሲሆኑ የፖለቲካል ሳይንስና ፍልስፍና ተመራማሪ ናቸው። ተመራማሪው ለኢዜአ እንዳሉት፤ በአገሪቱ የዜጎች ሰብዓዊ መብትን ማስጠበቅ ላይ የተሰራው ሥራ በቂ አይደለም። “በፊት ከነበሩ ሥርዓቶች አኳያ የተሻለ ነው፤ አሁን ካለው ሕገ-መንግሥት ድንጋጌዎች ሲታይ ግን ብዙ ይጎድላል'' ይላሉ። በሕገ-መንግሥቱ የሰፈሩ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ምን ያህል ሥራ ላይ ውለዋል ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል'' ያሉት አቶ ግደይ ድንጋጌዎቹ ወደ ተግባር የተቀየሩበትም፤ ያልተቀየሩበትም ቦታዎች አሉ በማለት ይሞግታሉ። የብሄር ብሄረሰቦች መብት መረጋገጡ፣ በቋንቋቸው የመጠቀምና ሃብት የማፍራት መብት በአንጻራዊነት መከበሩን በበጎ ጎኑ ያነሱት ተመራማሪው መንግሥት በመርህ ደረጃ ሰብዓዊ መብትን ተቀብሏል መተግበር ላይ ግን ሰፊ ክፍተት አለበት ብለዋል። እንደ አቶ ግደይ ገለጻ ሰብዓዊ መብት በአግባቡ እንዳይከበር ካደረጉ ምክንያቶች መካከል የፍትህ ተቋማት በሚጠበቅባቸው ደረጃ አለመስራት ተጠቃሽ ነው። አቶ ግደይ እንደሚገልጹት ሰብዓዊ መብት እንዲከበር መንግሥት ያደረገው ጥረት ባይካድም የሰው ህይወት መጥፋት፣ ዜጎች ከኖሩበት ቀዬ መፈናቀላቸው፣ ንብረታቸው መውደሙ አሁንም ቀሪ የቤት ሥራዎች እንዳሉ አመላካች ናቸው። የመንግሥት አካላት ሰብዓዊ መብት እይታ የተስተካከለ አለመሆን፣ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ አስተዳደር አለመኖር፣ የሕዝብ ጥያቄ በአግባቡ አለመመለስ ለሚታዩ ችግሮች መንስኤ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል። በቀጣይ አዲሱ አመራር ያለፉትን ድክመቶች ለይቶ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ አለበት ብለዋል አቶ ግደይ። “ሰብዓዊ መብት ተከብሮ የተጠናከረ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ፓርላማው የአንበሳ ጥርስ ሊኖረው ይገባል'' ያሉት ተመራማሪው የዴሞክራሲ ተቋማትም ጥርስ ሊኖራቸው ያስፈልጋል ብለዋል። የመብት ባለቤት መንግሥት ሳይሆን ሕዝቡ መሆኑን ገልጸው ኀብረተሰቡ የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት ለመብቱ መታገል እንዳለበት አስገንዝበዋል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ እሸት ገብሬ እንደተናገሩት፤ "በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት መከበርና የማስከበር ሁኔታ በጥሩ ጅምር ላይ ነው ያለው"። በአገሪቱ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ክትትል ሲደረግ መቆየቱን የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሩ በሚታዩ ችግሮች ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ተግባራት እንደተከናወኑ አስረድተዋል። ባለፉት ዓመታት ኮሚሽኑ ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ አካላት ማለትም ሴቶች፣ ህጻናት፣ አካል ጉዳተኞችና አረጋዊያን የመሳሰሉት ላይ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን አብራርተዋል። ተቋሙ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አቅም የሌላቸውና የሕግ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች ድጋፍ መስጠት መጀመሩን ገልጸው በዚህም ከ12 ዩኒቨርሲቲዎችና ከሁለት ድርጅቶች ጋር ተባብሮ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል። የኀብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን ተተርጉሞ በአምስት ቋንቋዎች ታትሞ መሰራጨቱንም ገልጸዋል። የተቋሙን ተደራሽነት ለማስፋትም የራሱን ፖርታል ከመዘርጋት ጀምሮ ነጻ የስልክ መስመሮችን በመጠቀም አገልግሎት የሚያገኝበት ስርዓት ተዘርግቷል ነው ያሉት። “ከዜጎች መብት ጋር በተያያዘ ሕገ-መንግሥቱ ምን ይላል የሚለው በበቂ መጠን ግንዛቤ አልተፈጠረም'' ያሉት አቶ እሸት ተቋማትም ሰብዓዊ መብት ላይ በአግባቡ እየሰሩ አይደለም ብለዋል። በአዋጅ ቁጥር 210/1992 ዓ.ም የተቋቋመው ኮሚሽኑ ስለ ሰብዓዊ መብት ኀብረተሰቡን የማስተማር፣ ሰብዓዊ መብቶች እንዳይጣሱ መከላከልና ተጥሰው ሲገኙ በሕጉ መሰረት እንዲታረሙ የማድረግ ኃላፊነቶች ተሰጥቶታል።