የቤተክርስቲያኗ እምነት ተከታይ የጥምቀት በዓልን በተለመደው አንድነትና በሰላማዊ መንገድ እንዲያከብር ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የቤተክርስቲያኗ እምነት ተከታይ የጥምቀት በዓልን በተለመደው አንድነትና በሰላማዊ መንገድ እንዲያከብር ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ ጥር 7/2011 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች መጪውን የጥምቀት በዓል በተለመደው አንድነትና በሰላማዊ መንገድ እንዲያከብር የሃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ፡፡
የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ከሚከበሩ የአደባባይ በዓላት አንዱ ሲሆን የህዝቦች ፍቅርና አንድነት ጎልቶ የሚንጸባረቅበት ነው፡፡
ህጻናት ከወጣቶች፣ አዛውንቶች ከልጆቻቸው ጋር ሆነው በአንድነትና በፍቅር ስሜት የሚታደሙበት ይህ በዓል ሃይማኖታዊ መሰረቱን ይዞ ባህላዊ ትርዒቶችና አልባሳት የሚታዩበት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሃይማኖት አባቶች እንደገለጹት፤ በዓሉ ሰላምን የሚያበስርና እንድነትን የሚያጠናክር በመሆኑ ቤተ ክርስትያኗ ሰፊ ዝግጅት አድርጋለች፡፡
የቤተክርስቲያኗ የውጭና አለምአቀፍ ግንኙነት ሃላፊ ብጹዕ አቡነ አረጋዊ (ዶ/ር) የበዓሉ በሰላም መከበር ለአገር ገጽታ ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል።
የሃይማት አባቶቹ አያይዘውም የጥምቀት በዓል ሰላምና ፍቅር የሚገለጽበት በመሆኑ ከሃገር በተጫማሪ አለም ዓቀፋዊ አስተዋጽኦው የጎላ ነው ፡፡
የቤተክርስቲያኗ የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ መጋቤ ሰላም ሰለሞን ቶልቻ የጥምቀት በዓል ለአገራዊ አንድነት ለአገራዊ ሰላም ፋይዳው ብዙ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በርካቶች በአሉን ለማክበር ከውጭ የሚመጡ እንደሆነ ይህንንም ተከትሎ በቱሪዝም ዘርፉ በርካቶች ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል፡፡
በጹዕ አቡነ አረጋዊ (ዶ/ር) በበኩላቸው የጥምቀት በዓል የተጣሉ የሚታረቁበት መለያየት የተወገደበት በዓል ነው ያሉት የሃይማኖት'' አባቶቹ፤ የኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ መጠመቅ ትህትናን እና ፍቅርን የሚስተምር በመሆኑ በዓሉን ሁሉም የእምነቱ ተከታይ በአንድነትና በሰላማዊ መንገድ እንዲያከበር ጥሪአቸውን አቅርበዋል፡፡
ጥምቀት ከሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቱ ባለፈ ለህዝቦች አብሮነትና መቻቻል ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው።