በፕሪሚየር ሊግ ተስተካካይ ጨዋታ ፋሲል ከተማ ደደቢትን በማሸነፍ ደረጃውን ወደ አምስተኛ ከፍ አድርጓል

99

አዲስ አበባ ጥር 7/2011 በ2011 ዓ.ም በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በተካሄደ ተስተካካይ ጨዋታ ፋሲል ከተማ ደደቢትን 2 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

በጎንደር ስታዲየም በተደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ፋሲል ከተማ በሙጂብ ቃሲምና በናይጄሪያዊው ኤዲ ቤንጃሚን ግቦች አሸናፊ ሆኗል።

ለደደቢት ከመሸነፍ ያዳነቸውን ግብ እንዳለ ከበደ ከመረብ አሳርፏል።

በውጤቱ መሰረት ፋሲል ከተማ ነጥቡን ወደ 15 በማሳደግ ከነበረበት ስምንተኛ ወደ አምስተኛ ደረጃ ከፍ ያለ ሲሆን በአንጻሩ ደደቢት በ3 ነጥብ የመጨረሻውን 16 ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የዛሬው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በስምንተኛ ሳምንት በጎንደር ስታዲየም መካሄድ የነበረበት ቢሆንም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጨዋታውን ላልተወሰነ ጊዜ አራዝሞት እንደነበር የሚታወስ ነው።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ ቡና በ18 ነጥብ ሲመራ፣ ሃዋሳ ከተማ በ17 ነጥብ ሁለተኛ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ15 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ይዘዋል።

ስሑል ሽረ፣ ደደቡብ ፖሊስና ደደቢት ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።

የሊጉን ኮከብ አግቢነት የአዳማ ከተማው ዳዋ ሁቴሳና የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ በተመሳሳይ ሰባት ግቦች ሲመሩ፣ የመከላከያው ምንይሉ ወንድሙ በስድስት የሀዋሳ ከተማዎቹ እስራኤል እሸቱና ታፈሰ ሰለሞን በተመሳሳይ አምስት ግቦች ይከተላሉ። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም