ለኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት እንቅፋት ከሆኑት ዋናው አደረጃጀቱ ነው-የክለብ አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
ለኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት እንቅፋት ከሆኑት ዋናው አደረጃጀቱ ነው-የክለብ አመራሮች
አዲስ አበባ ጥር 7/2011 የኢትዮጵያን እግር ኳስ ለማሳደግ አሁን ያለው አደረጃጀት ፈርሶ በአዲስ መዋቅር ሊተካ እንደሚገባ ያነጋገርናቸው የክለብ አመራሮች ገለጹ።
በኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገትን ከማየት ይልቅ በስፖርታዊ ጨዋነት ችግር የሚታመስ ሆኗል።
ለችግሩ በርካታ ምክንያቶችን መጥቀስ ቢቻልም የሊጉ አደረጃጀት ዋነኛው መሆኑ ነው የተገለጸው።
እነዚህን ችግሮች ለመፍታትና የሀገሪቱን እግር ኳስ ለማሳደግ ውድድሮች በዞን ወይም በክልል ደረጃ እንደገና መዋቀር እንደሚገባው ነው ኢዜአ ያነጋገራቸው የክለብ አመራሮች የገለጹት።
በተለይም የራስ አቅም ያልፈጠሩና በመንግስት ወይም በሌላ አካል ላይ ጥገኛ የሆኑ ክለቦችን ከክልል ክልል ይዞ መዞሩ ትልቅ ችግር መሆኑን ያወሳሉ።
የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ አብነት ገብረመስቀል በሀገሪቷ ጠንካራ እግር ኳስ ሳይኖር የሊግ ፎርማት ይዞ ክለቦች ከክልል ክልል ተዛዋውረው እንዲጫወቱ ከማድረግ ይልቅ ውድድሮችን በዞን ደረጃ ማድረግ የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ነው የተናገሩት።
ይህ ደግሞ ጥቅሙ ክልሎች ላይ ጠንካራ እግር ኳስ እንዲኖርና ታዳጊዎችን በሰፊው ለማፍራት ከማገዙም በላይ ጠንካራ ብሄራዊ ቡድን ለመገንባትም ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው ብለዋል።
እግር ኳሱ የተሻለ እድገት እንዲኖረውና ክለቦች ህዝባዊ መሰረት እንዲኖራቸው ማድረግና ባለሀብቶችን ክለቦችን እንዲይዙ የሚያበረታታ ነገር ሊፈጠርላቸው እንደሚገባም ነው አቶ አብነት የተናገሩት ።
የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ ስንታየሁ በቀለ በበኩላቸው የእግር ኳስ ውድድሮች በዞን ወይም በክልል ደረጃ ቢደረግ የተሻለ አመራጭ እንደሆነና ይህም ክለቦች አሁን ከሚያወጡት ወጪ አንጻር የተሻለ ወጪ ቆጣቢ መሆኑን ነው ያስታወቁት።
አሁን ላይ ክለቦች በርካታ ኪሎ ሜትር አቋርጠው ከክልል ክልል ተዛውረው የሚጫወቱ በመሆኑ ለበርካታ ወጪ እየታደረጉ ነው ብለዋል።
ይሄ ደግሞ ክለቦች በፕሪሚየር ሊጉና በከፍተኛ ሊግ ደረጃ የሚያወጡት ወጪን በመቀነስ ገንዘቡን ለታዳጊ ስፖርተኞች ስልጠና እንዲያዋሉ ያግዛቸዋል ብለዋል።
ከዚህም በላይ በየክልሎቹ ክለቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከርና ክለቦቹ አቋማቸውን የሚፈትሹበት ከየክልል የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ጨዋታ ማድረግ እንደሚቻልም ነው የጠቆሙት።
የኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ስፖርት ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ እጅጉም አሁን ያለውን የሊግ አደረጃጀት በመቀየር ወደ ዞን ወይም ክልል በማውረድ አጠቃላይ ስፖርቱ ደግሞ በስፖርት ምክር ቤት ሊመራ ይገባል ነው ያሉት።
ውድድሮች በዞን ወይም በክልል ደረጃ ከተደረጉ እግር ኳሱን ከሚያቀጭጩ ነገሮች አንዱ የሆነውን የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር ለመፍታት እንደሚያግዝም ነው የገለጹት።
ከዚህ በተጨማሪ የስፖርታዊ ጨዋነት አንዱ የእግር ኳስ ችግር በመሆኑ የክለቦች ስያሜን መለወጥ እንደሚያስፈልግም ይናገራሉ።
ከዚህ በፊት በ1950ዎቹ ከጎሳ ጋር ስያሜ ያላቸው ክለቦች ችግር በመፍጠራቸው እንደገና ስያሜቸውን በድርጅት በማድረግ እንደተፈታ ያወሳሉ አቶ አብነት እና አቶ አሸናፊ።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ አዲሱ የሊግ ፎርማት በ1990ዓ.ም እንደተጀመረ ይታወሳል።