በሞጆ ከተማ የሚገኙ አራት ቆዳ ፋብሪካዎች እንዲዘጉ ተወሰነ

65

አዲስ አበባ ጥር 7/2011 በሞጆ ከተማ የሚገኙ አራት ቆዳ ፋብሪካዎች እንዲዘጉ ውሳኔ ተላለፈ።

ፋብሪካዎቹ እንዲዘጉ የተወሰነው ተረፈ ምርታቸውን ሳያጣሩ ወደ ወንዝ በመልቀቅ በአካባቢው ነዋሪዎችና በአየር ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሳቸው በመረጋገጡ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል የደን አካባቢና የአየር ለውጥ ባለስልጣን አስታወቋል። 

ባለስልጣኑ እንዳለው ከፌዴራል የደን፣ አካባቢና አየር ለውጥ ኮሚሽን ጋር በመሆን በሞጆ ከተማ በሚገኙ 12 የቆዳ ፋብሪካዎች ላይ ተደጋጋሚ ጥናት አካሂዷል።

በጥናቱ መሰረትም ፋብሪካዎቹ በተረፈ ምርታቸው ላይ ምንም ዓይነት የማጣራት ተግባር ሳያከናውኑ ወደ ወንዝ የሚልኩ መሆኑ ተረጋግጧል።

ዛሬ እንዲዘጉ ውሳኔ የተላለፈባቸው አራት ፋብሪካዎች በሂደት ላይ ያለ ምርታቸውን በ15 ቀን ውስጥ እንዲያጠናቅቁ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።

ተረፈ ምርታቸውን በከፊል የማጣራት ተግባር የሚያከናውኑ ሌሎች አራት ፋብሪካዎች ደግሞ የማጣራት አቅማቸውን የተሟላ ማድረግ እንዲችሉ የአንድ ወር ጊዜ ተሰጥቷቸዋል።

ቀሪዎቹ ሶስት ፋብሪካዎች ችግር የለብንም ቢሉም ችግር እንደሌለባቸው በጥናት ተረጋግጦ በሶስት ወር ውስጥ የጥናት ውጤቱ እንዲያቀርቡ መታዘዙን ነው በባለስልጣኑ የአካባቢ ህግ አስከባሪነት ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ስንታየሁ በፍቃዱ የተናገሩት።

ፋብሪካዎቹ ወደ ወንዝ የሚለቁት ፍሳሽ በሰው፣ በእንሰሳትና በአካባቢ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በከተማዋ ካሉት የቆዳ ፋብሪካዎች ውስጥ አንዳቸውም የአካባቢ ጥበቃ ደህንነትን እንዳማያሟሉ የተናገሩት አቶ ስንታየሁ ችግሩ እስኪፈታ ክትትልና ቁጥጥሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አሳስበዋል።

እንዲዘጉ ትዕዛዝ የተላለፈባቸው ፋብሪካዎችም ችግራቸውን ሳያስተካክሉ ስራ እንደማይጀምሩ ነው ያስታወቁት።

ይሁንና የፋብሪካዎቹ ሰራተኞች ፋብሪካዎቹ ያለባቸውን ችግር አስተካክለው ወደስራ እስኪገቡ ድረስ የወር ደመወዛቸው እንዳይቋረጥ ይደረጋል ተብሏል።

በኢትዮጵያ ከ32 በላይ የቆዳና ሌጦ  ኢንዱስትሪዎች እንዳሉ ይነገራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም