በከተማዋ ባለፉት ስድስት ወራት ከ2ሺ በላይ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያና ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ መያዙ ተገለጸ

አዲስ አበባ ጥር 7/2011 በአዲስ አበባ ባለፉት ስድስት ወራት ከ2ሺ በላይ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች፣ ከ50 ሺህ በላይ ጥይቶችና ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እንደተያዘ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ህገ-ወጥና ሀሰተኛ የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል በተከናወነው ተግባር የተለያዩ አገሮች የገንዘብ ኖት መያዙን ኮሚሽኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ ጠቅሷል፡፡   

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እንዲሁም ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ ህገ-ወጥና ሀሰተኛ ገንዘብ ዝውውር ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።

ከሀምሌ 2010 እስከ ታህሳስ 2011 ዓ.ም ባለው ስድስት ወር በተደረገው ክትትል 2 ሺህ 383 ልዩ ልዩ የጦር መሳሪያዎችና  56 ሺህ 615 ጥይት በቁጥጥር ስር አውሏል።

ከተያዙት የጦር መሳሪያዎች መካከል ሁለት የእጅ ቦንብና አንድ መትረየስ ይገኝበታል።

የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎቹ የተሽከርካሪ አካል በመፍታትና የተሽከርካሪ አካል ላይ መሸሸጊያ በመስራት እንዲሁም ከሌሎች ዕቃዎች ጋር በማመሳሰል የጦር መሳሪያ ሲያዘዋወሩ መያዛቸው ተጠቁሟል።

በተጨማሪ ባለፉት ስድስት ወራት ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል በተሰራው ስራ 68 ሚሊዮን 322 ሺህ 344 ብር፣ 88 ሺህ 151 የአሜሪካ ዶላር፣ 9 ሺህ 480 ዮሮ ፣ 12ሺህ 620 ፓውንድና  የሌሎች አገሮች የገንዘብ ኖት መያዙን ኮሚሽኑ ገልጿል።

በህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች አብዛኛውን ጊዜ ወንጀሉን የሚፈፅሙት በህጋዊ ንግድ ከለላ እንደሆነና አብዛኞቹ  የስጦታ እቃ፣ ቡቲክ፣ ባርና ሬስቶራንት የሚል ፈቃድ በማውጣት በመሆኑ እንደሆነ መግለጫው አመልክቷል።

በህገወጥ የገንዘብ ዝወውር አንዳንድ የውጪ ዜጎች ተሳትፎ እንደነበራቸው በምርመራ ተረጋግጧል።

ሀሰተኛ የገንዘብ ዝውውር ለመከላከል በተሰራው ስራ 163 ሺህ 600 ብር እና 3 ሺህ 800 የአሜሪካ ዶላር መያዙም ተገልጿል።

ህብረተሰቡ ይህንኑ ተገንዝቦ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ያመለከተው ፖሊስ ኮሚሽኑ በህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ተሳትፎ ያደረጉ አካላት ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ለፖሊስ አባላት መደለያ ሲሰጡ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ገልጿል።

ፖሊስ ይህንን ተግባር ሲያከናውን ህብረተሰቡ ጥቆማና ምስክርነት በመስጠት የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ያስታወሰው መግለጫው ከፖሊስ ጎን በመሆን የሚያደርገውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፖሊስ ጥሪ የሚያቀርብ መሆኑን አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም