ቀጥታ፡

ባለፉት ስድስት ወራት ከቡና የወጪ ንግድ 3 መቶ 33 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ 7/2011 የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ባለፉት ስድስት ወራት ከቡና የወጪ ንግድ 3 መቶ 33 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ ህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ከሐምሌ እስከ ታህሳስ 131 ሺህ 400 ቶን የቡና ምርት ለመላክ ታቅዶ 103 ሺህ 100 ቶን መላክ ተችሏል።

አፈፃፀሙ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በመጠን 4 ሺህ ቶን በገቢ ደግሞ የ47 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ አሳይቷል።

በነሐሴ ወር 93 በመቶ ከፍተኛ ሽያጭ ሲመዘገብ በህዳር ወር ደግሞ 62 በመቶ በመሆን ዝቅተኛ ሽያጭ ተመዝግቦበታል።

በ2011 በጀት ዓመት ታህሳስ ወር ከ18 ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት በመላክ 66 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 12 ሺህ 991 ቶን የቡና ምርት በመላክ ከዕቅዱ 69 በመቶ መሳካቱንም መግለጫው አመልክቷል።

የታህሳስ ወር አፈፃፀም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በመጠን 14 በመቶ እና በገቢ 20 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።

የኢትዮጵያን የቡና ምርት በመግዛት ሳውዲ አረቢያ፣ጀርመን እና ጃፓን ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃን ይዘዋል።

በተያያዘ ዜና ባለፉት ስድስት ወራት የቅመማ ቅመም ወጪ ንግድ ክንዉን በመጠን 4 ሺህ 368 ቶን ወደ ውጪ ተልኮ 4 ሚሊዮን 940 ሺህ  የአሜሪካን ዶላር ተገኝቷል።

ይህ አፈፃፀም ከእቅዱ ጋር ሲነፃፀር በመጠን የ60 በመቶ እና በገቢ የ49 በመቶ አፈፃፀም በመሆን ተመዝግቧል፣ይህ ማለት ከዕቅዱ አንፃር በመጠን የ39 በመቶና በገቢ የ50 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።

የዘንድሮው ስድስት ወራት አፈፃፀም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወሮች ጋር ሲነፃፀር በገቢ 970 ሺህ ዶላር ቅናሽ አሳይቷል።

የኢትዮጵያን ቅመማ ቅመም በመግዛት ህንድ፣ሱዳን እና ኢንዶኖዥያ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ መያዛቸውን መግለጫው አመልክቷል።

በበጀት ዓመቱ ከሐምሌ እስከ ታሕሣሥ 984 ቶን የሻይ ምርት ወደ ውጪ ተልኮ 1 ሚልዮን 650 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ተገኝቷል።

የእቅዱ አፈፃፀምም በመጠን የ65 በመቶ እና በገቢ የ53 በመቶ ሲሆን በመጠን የ34 በመቶ እና በገቢ የ46 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።

ያለፉት ስድስት ወራት ክንውን ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በመጠን 92 ቶን እና በገቢ ደግሞ 480 ሺህ ዶላር ቅናሽ ማሳየቱን የባለስልጣኑ መረጃ አመልክቷል።        

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም