የንግድ ትርኢትና ባዛር በጎንደር ከተማ ተከፈተ - ኢዜአ አማርኛ
የንግድ ትርኢትና ባዛር በጎንደር ከተማ ተከፈተ
ጎንደር ጥር 6/2011 የፋሲል ከነማን የእግር ኳስ ቡድን በገንዘብ ለመደገፍ የተዘጋጀ የንግድ ትርኢትና ባዛር ዛሬ በጎንደር ከተማ ተከፈተ፡፡
የዝግጅቱ አስተባባሪ አቶ ጋሻው አስማረ እንደተናገሩት በንግድ ትርኢትና ባዛሩ ከ200 በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ነጋዴዎች እየተሳተፉበት ነው፡፡
የሀገር ውስጥ ነጋዴዎች ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ከውጪ ደግሞ ከፊሊፒንስና ህንድ የመጡ ናቸው፡፡
ከጥምቀት በዓል ጋር ተያይዞ የተዘጋጀ መሆኑን አመልክተው ዝግጅቱን አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ እንደሚጎበኘው የሚጠበቅ መሆኑን አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡
ከተሳታፊ ነጋዴዎች መካከል ወይዘሮ ፌቨን ጌታቸው በሰጡት አስተያየት ከአዲስ አበባ እንደመጡና የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን እንዳቀረቡ ተናግረዋል የእስካሁኑ እንቅስቃሴም ጥሩ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
የእንጨት ስራ ውጤቶችን በተለይ በጎንደር ግንብ የተቀረፁ ስራዎችን ብዙ ተጠቃሚ እንደገዟቸው የተናገሩት ደግሞ ከጅማ የመጡት አቶ አልዓዛር ጀቤሳ ናቸው፡፡
ከሽያጩ ተጠቃሚ ከመሆኑ ባለፈ ታሪካዊ ከተማ የሆነችው ጎንደር ለመጀመሪያ ማየትና የጥምቀት በዓል ላይ መታደም በተፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡
የስፖርት እቃዎችን በማቅረብ ከህንድ ነጋዴዎች ውስጥ ተሳታፊ የሆኑት ሚስተር ፓቴል ሻርማን በበኩላቸው ባዛሩ ሞቅ ደመቅ ያለ እንደሆነና ብዙ ጎብኝዎች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡
" ያቀርብኳቸውን የስፖርት እቃዎች በመሸጥ ተጠቃሚ ሆኛሉሁ፤ የከተማዋ ህዝብ የእንግዳ አቀባበልም ደስ የሚል ነው" ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ፣ በሃዋሳና በአክሱም በነበሩ የንግድና ባዛር ትርኢት ላይ ተሳታፊ እንደነበሩ አስታውሰው ጎንደር ለመጀመሪያ ጊዜ እንደመጡና ታሪካዊ ቅርሶችን በመጎብኘት ጥሩ ጊዜ እያሳለፉ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡
የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን ሲገዙ የኢዜአ ሪፖርተር ያገኘናቸው ወይዘሮ ሽዋ አባይነህ በሰጡት አስተያየት "ጎንደር በቀላሉ ገበያ ላይ የማናገኛቸውን እቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ከዚህ በማግኘቴ ተደስቻለሁ" ብለዋል፡፡
ወጣት አፎሚያ አምሳሉ በበኩሏ የመዋቢያ እቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋና በአንድ ቦታ መግዛት መቻሏን ተናግራለች፡፡
የንግድ ትርኢትና ባዛሩ ዝግጅት እስከ ጥር15/2011 ዓ.ም. የሚቆይ ሲሆን በዚህም የስፖርት ክለቡ ከሶስት ሚሊዮን 500ሺህ ብር በላይ ገቢ እንደሚገኝ ይጠበቃል፡፡