ሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኘው ለ2 ጊዜ ክስ ተመሰረተባቸው - ኢዜአ አማርኛ
ሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኘው ለ2 ጊዜ ክስ ተመሰረተባቸው
አዲስ አበባ ጥር 6/2011 ሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኝው ለሁለተኛ ጊዜ ክስ ተመሰረተባቸው።
ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘውን ጨምሮ የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ /ሜቴክ/ የቀድሞ ሰራተኞች በመንግስትና ህዝብ ላይ የ544 ሚሊዮን 772 ሺህ 623 ብር ጉዳት አድርሰዋል ሲል ዐቃቤ ህግ በከባድ የሙስና ወንጀል ከሷቸዋል።
በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ክስ የተመሰረተባቸው ሜጄር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው፣ ኮሎኔል በርሄ ወልደሚካኤል (ያልተያዘ)፣ ኮሎኔል ሙሉ ወልደገብርኤል ፣ ብርጋዴር ጄኔራል ጠና ቁሩንዲ፣ ኮሎኔል ተከስተ ኃይለማርያም፣ አቶ ሰለሞን ኃይለሚካኤል (ያልተያዘ) እንዲሁም ኮሎኔል መሐመድ ብርሃን ናቸው።
በተጨማሪም ኢብራሂም ሀጎስ (ያልተያዘ)፣ ሻለቃ ሰለሞን አብርሃ ፣ ኮሎኔል ዓለሙ ሽመልስ ፣ ኮሎኔል አዜብ ታደሰ ፣ ሻምበል ይኩኖአምላክ ተስፋዬ፣ ሻምበል ሰመረ ኃይሌ ፣ ሚስተር ሞህድ ራፍ (ያልተያዘ) እንዲሁም አቶ ኡስማን አብዱም (ያልተያዘ) ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ዐቃቤ ህግ በተጠርጣሪዎቹ ላይ የመሰረተው ክስ የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ከ28 ዓመታት በላይ የተገለገለባቸውን አባይ ወንዝ እና አብዮት በተባሉ ሁለት መርከቦች ግዢ ጋር በተያያዘ ተፈጽሟል ባላቸው የሙስና ወንጀል ነው።
ተጠርጣሪዎቹ መርከቦቹን በ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር እንዲገዙ በማድረግ በ7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ዕድሳት ተደርጎላቸው ሥራ እንዲጀምሩ ያደረጉ ሲሆን በመርከቦቹ ትርፍ ሳይሆን ኪሳራ እንዳደረሱ በክሱ ተጠቅሷል።
መርከቦቹ አዋጭ ባለመሆናቸውም በኪሳራ 607 ሺህ 432 ዶላር በመሸጣቸው በመንግሥትና በህዝብ ላይ የ544 ሚሊዮን 772 ሺህ 623 ብር ጉዳት መድረሱን የዐቃቤ ህግ የክስ ጭብጥ ያስረዳል።
ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ህግ ያቀረበውን ክስ በንባብ ያሰማ ሲሆን የተከሳሾችን የክስ መቃወሚያ ለመቀበል ለጥር 20 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ሜጄር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው፣ በሜቴክ ሥር ለሚገኘው የአዳማ እርሻ መሣሪያዎች ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ አገልግሎት የሚውሉ ትራክተሮች ግዥ በተካሔደበት ወቅትም፣ ከኮርፖሬሽኑ የግዥ አፈጻጸም መመሪያ ውጭና ያለጨረታ ግዢ እንዲፈጸም በማድረግ ወንጀል ጥር 2 ቀን 2011 ዓ.ም አቃቤ ሕግ ክስ እንደመሰረተባቸው የሚታወቅ ነው።