የህክምና ተቋማቱ ለህብረተሰቡ የተሟላ አገልግሎት ሊሰጡ ይገባል ---ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
የህክምና ተቋማቱ ለህብረተሰቡ የተሟላ አገልግሎት ሊሰጡ ይገባል ---ቋሚ ኮሚቴው
አዳማ ጥር 7/2011የአዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅና የአዳማ ከተማ ጤና ጣቢያ ለህብረተሰቡ የተሟላ አገልግሎት ሊሰጡ እንደሚገባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
ቋሚ ኮሚቴው ባለፉት ሶስት ቀናት በተቋማቱ ላይ ተገኝቶ ላደረገው የመስክ ምልከታ ዛሬ ግብረ መልስ ሰጥቷል።
የቋሚ ኮሚቴው ቡድን መሪ አቶ ዘላለም ታረቀኝ እንደገለጹት ቋሚ ኮሚቴው በሁለቱ ተቋማት በመገኘት ህብረተሰቡ በምን መልኩ የጤና አገልግሎት እያገኘ እንደሆነ ተመልክቷል።
"ተቋማቱ ባላቸው ውስን የሰው ኃይል የተሻለ አገልግሎት ለህብረተሰቡ እየሰጡ መሆናቸውን ቋሚ ኮሚቴው በጠንካራ ጎን አይቷል" ብለዋል።
በሰራተኞች መካከል ያለው የእርስ በእርስ መደጋገፍ፣ የዘርፈ ብዙ ምላሽ ስራዎችንና ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለማቃለል የተጀመሩ ስራዎችንም በተቋማቱ ሌላው የታዩ ጠንካራ ጎኖች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ቋሚ ኮሚቴው በአዳማ ጤና ጣቢያ ላይ በድክመት ካነሳቸው ጉዳዮች መካከል ህሙማንን አስተኝቶ የህክምና አገልግሎት መስጠት አለመቻሉ ተጠቃሽ ነው።
ጤና ጣቢያው ከ80 ሺህ ለሚበልጥ ህብረተሰብ አገልግሎት እየሰጠ አምቡላንስ አለመኖሩ ሌላው ድክመት መሆኑን ጠቅሰዋል።
"ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ የትርፍ ሰዓት ክፍያ ለጤና ባለሙያዎች ማቆሙ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ማሳደሩንም ቋሚ ኮሚቴው ተመልክቷል" ብለዋል።
በአዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ በድክመት ከታዩ መካከል የሰው ኃይልና የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት ዋና ዎቹ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
"ተቋሙ ለህክምና ባለሙያዎች የትርፍ ሰዓት ክፍያ እየፈጸመ ለአስተዳደርና ፋርማሲ ሰራተኞች መንፈጉ በአጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴው ላይ እንቅፋት መፍጠሩን ኮሚቴው ተገንዘቧል " ብለዋል።
የስራው ባህሪ አስቸኳይ የመዳኃኒት ግዥ እንደሚያስፈልገው እየታወቀ የቀጥታ መደኃኒት ግዥ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ከመሆኑም ባለፈ የ5ሺህ ብር ግዥ ብቻ እንዲፈፀም መወሰኑ ድክመት መሆኑን ጠቁመዋል።
ለሆስፒታሉ የተሻሉ ባለሙያዎች ቢመደቡም የህክምና መርጃ መሳሪያዎች እጥረት ህብረተሰቡ የተሟላ አገልግሎት ማግኘት ካለመቻሉም ሌላ ባለሙያዎችም ስራ እየለቀቁ ስለመሆናቸው ቋሚ ኮሚቴው መገንዘቡን አስረድተዋል።
በነርስ ባለሙያ እጥረት ሆስፒታሉ ወላድ እናቶችን ተቀብሎ በአግባቡ አለማስተናገዱ አንገብጋቢ ችግር መሆኑን ጠቁመዋል።
"የኮሌጁ መዋቅር በአግባቡ ያልተጠናና የውስጥ ሰራተኛውን ያላሳተፈ መሆኑ ሰራተኛውን ለቅሬታ ዳርጎታል" ብለዋል።
የኮሌጁ የህክምና ተማሪዎች መማሪያ ክፍል በግለሰብ ኪራይ ቤት መሆኑ ደህንነታቸው ተጠብቆ የተሟላ ትምህርት እንዳያገኙ እንቅፋት መሆኑም ኮሚቴው መመልከቱን አንሰተዋል።
ተቋማቱ ድክመቶቻቸውን በመፍታት ለህብረተሰቡ የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት በአሰራር ስርዓት ተደግፈው ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
ከተቋማቱ በላይ የሆኑ ችግሮችን ቋሚ ኮሚቴው ከሚመለከታቸው የበላይ አካላት ጋር በመምከር ለመፍትሄው እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
የአዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅና የአዳማ ከተማ ጤና ጣቢያ የስራ ኃላፊዎች በበኩላቸው ቋሚ ኮሚቴው በድክመት ያነሳቸውን ጉዳዮች በግብዓትነት በመውሰድ ለመፍትሄው እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።
የህብረተሰቡ ፍላጎት ሰፊ ቢሆንም አንዳንዶቹ ጉዳዮች በተያዘው ዓመት ውስጥ እልባት እንደሚያገኙ የተቋማቱ የስራ ኃላፊዎች አመላክተዋል።