ቀጥታ፡

ዲፕሎማቶች አገራዊ ተልዕኳቸውን በውጤት ለመደገፍ መስራት አለባቸው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ

አዲስ አበባ ጥር 6/2011 ኤምባሲዎች አገራዊ ተልዕኮዎች የሚፈጸሙባቸው እንጂ የመዝናኛና እረፍት ቦታዎች ባለመሆናቸው ዲፕሎማቶች ተልዕኳቸውን በውጤት ለመደገፍ መስራት አለባቸው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አሳሳቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት ተልዕኳቸውን በአግባቡ የማይወጡ ዲፕሎማቶችን ከዚህ በኋላ እንደማይታገስም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት  "ዓለም ዓቀፍ አዝማሚያዎችና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ" በሚል ርዕስ  በኢትዮጵያ ሚሲዮኖችና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሚሰሩ ዲፕሎማቶች ዛሬ ገለፃ ባደረጉበት ወቅት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ኤምባሲዎች የሚሰሩ ዲፕሎማቶች በውጤት ስለማይለኩ ፋይዳ በሌለው ስራ ተጠምደው ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ።

ኤምባሲ የጡረታ ማስከበሪያና የማረፊያ ቦታ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዲፕሎማቶች ከዚህ በኋላ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በውጤት ለመደገፍ ሊታትሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ባለፉት ጊዜያት የነበሩ ዲፕሎማቶች ከትልቁ አገራዊ ተልዕኮ ከማስፈጸም ይልቅ ለሚደግፉት ቡድንና ሁኔታ የመስራት አዝማሚያ እንደነበራቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በመሆኑም መንግስት ከዚህ በኋላ ተልኳቸውን በአግባቡ መፈጸም የማይችሉ ዲፕሎማቶችን አይታገስም ብለዋል።

አምባሳደሮች ወደ ተለያዩ አገሮች ሲመደቡ በዙውን ጊዜ ጭቅጭቅ እንደሚፈጠር ጠቁመው፤ ይህም ትልቅ የሚባለውን አገርን ከመሸከም ይልቅ የራስ ምቾትና ተድላን ማሳደድን ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

ኃላፊነት የሚፈተነው በምቾት ሳይሆን በችግር ውስጥ በመሆኑ ዲፕሎማቶች ይህን ተገንዝበው የአገር እንደራሴነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው ምክረ ሃሳብ ሰንዝረዋል።

ዲፕሎማቶች በአሁኑ ጊዜ ብዙሃኑን እያሸነፈ ካለው የእኔነት ስሜት መውጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ "ኢትዮጵያ ያለችበት ቀጠና የበርካታ ኃያላን መንግስታትን ቀልብ የሳበ ከመሆኑ አንጻር ከእኔነት ወጥተን ከጎረቤቶቻችን ጋር ኢኮኖሚያዊ ውህደት መፍጠር አስፈላጊ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

ዲፕሎማቶች እራሳቸውን ከዓለም ሁኔታ ጋር ለማጣጣም የህይወት ዘመን ተማሪዎች መሆን እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል።

መንግስት የዲፕሎማሲ ስራውን አሁን ካለው  አገራዊና የዓለም ዓቀፋዊ ሁኔታ ጋር ለማጣጣም የውጭ ግንኙነት ፖለሲውን እንደሚያሻሽልም  ጠቅላይ ሚኒስትሩ አውስተዋል።

በኢትዮጵያ የአምባሳደሮች ሹመት በርካታ ጥያቄ ይነሳበት እንደነበር ይታወሳል።

በተለይም በአገር ውስጥ በከፍተኛ የስራ ሃላፊነት የነበሩ ሰዎች በተለያየ ምክንያት ከሃላፊነት ሲነሱ አምባሳደር እየተደረጉ መሾማቸው በርካታ ትችት ይሰነዘርበት ነበር።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቅርቡ ይፋ እንዳደረገው የአምባሳደሮች ሹመት በዕውቀት ላይ ተመስርቶ እንደሚሆን ተነግሯል።

ይህንን ተከትሎ በቅርቡ  የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር 19 አዲስ ተሿሚ አምባሳደሮች ኢትጵያን ወክለው የሚሰሩባቸውን አገሮች ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም