ቀጥታ፡

በአልነጃሺ ያለውን ታሪክ ለመስህብነት ለማዋል ጥረት እየተደረገ ነው

መቀሌ  ጥር 6/2011 በትግራይ ክልል አልነጃሺ ያለውን  ታሪክ ስፍራ ለዓለም ህዝብ በማስተዋወቅ ለመስህብነት ለማዋል ጥረት እየተደረገ  መሆኑ ተገለጸ፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሶስት ሀገራት የተውጣጡ የእስልምና ኃይማኖት መሪዎች በተገኙበት ትናንት የአልነጃሺ ታሪክን ለማስተዋወቅ በስፍራው የፀሎት እና ሌሎች የእምነቱ ስነስርዓቶች ተካሂደዋል።

በዚህ ወቅት እንደተገለጸው ታሪካዊ ስፍራውን  ለማስተዋወቅ ቢሞከርም የተጠናከረ ባለመሆኑ መስህቡ በጎላ መልኩ  ጥቅም ላይ  አልዋለም።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዩች  ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ መሐመድ አሚን ጀማል ኢትዮጰያ ከአልነጃሺ ጊዜ ጀምሮ የሰላምና የመከባበር መሰረት እንዲሁም የኃይማኖት ነፃነት የታየባት ድንቅ ሃገር  መሆኗን ተናግረዋል፡፡

ታሪካዊ ስፍራው የሰይድ አህመድ አልነጃሽ መካነመቃብ ብቻ ሳይሆን እስከ 15 የሚሆኑ የነቢዩ ሰሓቦች/የስራ ባልደረቦች/ መካነመቃብራቸው የሚገኝበት መሆኑንም አመላክተዋል።

" ወደ ስፍራው የበርካታ ሙስሊም አገራት የእምነቱ ተከታዮች ለመምጣት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው"  ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣በየጊዜው ጥያቄ እያቀረቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በምስራቃዊ ዞን ክልተ አውላዕሎ ወረዳ የሚገኘው የአልነጃሽ መስጊድ ከ1 ሺህ 400 ዓመታት በፊት የነቢዩ መሓመድ ተከታዩች መጥተው ያረፉበት ቅዱስ ስፍራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሺህ አደም አብደል ቃድር ናቸው።

ይህን ታሪካዊ ስፍራ ለማስተዋወቅ የሚደረጉ ሙከራዎች ቢኖሩም የተጠናከረ ባለመሆኑ መስህብነቱ በጎላ መልኩ  ጥቅም ላይ እንዳልዋለ ገልጸዋል።

" የአልነጃሺ ታሪክ የትእግስትና የመቻቻል፣ የአብሮነትና ለሰው ልጅ ክብር መስጠትን የምንማርበት ነው" ብለዋል።

በተለይ ወጣቱ ትውልድ ከዚህ ታሪካዊ ስፍራ በሰው ልጆች መካከል ልዩነት ሊደረግ እንደማይገባ በተግባር ሊማርበት የሚገባ መሆኑን ሼህ  አደም አመልክተዋል።

የኢትዮ ነጃሽ ፕሮሞሽን ዳይሬክተር መምህር ያሲን ራጂኡ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት በሀገር አቀፍ ደረጃ ኢትዮ- ነጃሽን የሚያስተዋውቅ አካል መቋቋሙን አስታውቀዋል።

የመጀመሪያ ስራ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት  በመሆን በሀገሪቱ ወደሚገኙ መስጊዶች ስለአልነጃሺ ዝርዝር መረጃ እንዲሰራጭ የመደረጉን ያስታወሱት መምህር ያሲን፣በአረብ አገራት የማስተዋወቅ ስራ መካሄዱን አስረድተዋል።

ከቱርክ መንግስትና የኃይማኖት አባቶች ጋር በተካሄዱ የውይይት መድረኮችም ከገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ በየዓመቱ እስከ 200ሺህ የኃይማኖቱ ተከታዮቸ ወደ አልነጃሽ ለማምጣት ቃል የተገባላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በአልነጃሺ ዙሪያ ከ30 ዓመታት በላይ ጥናትና ምርምር እንዳካሄደ የገለጹት ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል ፋሪስ   " አልነጃሺ ካለው ታሪክ አንፃር እስካሁን  ለቱሪዝም መስህብነት አልተጠቀምንበትም "ብለዋል።

አልነጃሺ ከኃይማኖታዊ ተልዕኮው በበለጠ ሀገራዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸው መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት የቱሪዝም ዘርፍን ሊያጎለብት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በስነ ስርዓቱ ወቅት ከኢትዮጰያ የተለያዩ ስፍራዎች፣ከሱዳንና ኤርትራ  የመጡ  የኃይማነቱ መሪዎችና  አባቶች ተገኝቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም