ቀጥታ፡

ክለቡ በስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት የሚከሰቱ ግጭቶችን እንዲያርም ተጠየቀ

ሶዶ ጥር 5/2011 የወላይታ ድቻ ስፖርት ክለብ በስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት ምክንያት የሚከሰቱ ግጭቶች ለማረም ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ፡፡

ክለቡ ዘጠነኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ዛሬ በወላይታ ሶዶ ከተማ አካሂዷል።

የክለቡ ደጋፊዎች በዚሁ ወቅት ስፖርት ወዳድ የሆነዉን የአካባቢውን ማህበረሰብና ደጋፊዎችን ዋጋ እያስከፈለ በስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት የሚከሰቱ ግጭቶችና መሰል ድርጊቶችን ለማረም ትኩረት ሰጥቶ መስራት አለበት ተብሏል፡፡

በሶዶ ሁለገብ ስታዲየም በሚካሄዱ ጨዋታዎች ሳቢያ የሚፈጠሩት ረብሻዎች ሜዳውንም ሆነ ክለቡ ለቅጣት መዳረጋቸው በጥበቅ ሊታሰብበት  እንደሚገባ ተሳታፊዎቹ አመልክተዋል፡፡

የወጣላቸውን ገንዘብ የማይመጥን እንቅስቃሴ የሚያደርጉ፣የሚጠበቅባቸውን ሳይወጡና ከአቅም በታች በመጫወት ለቡድኑ ውጤት መዋዠቅ ምክንያት የሚሆኑና ከተቃራኒ ቡድን ጋር አላስፈላጊ መጎሻሸም ውስጥ በመግባት  ስፖርታዊ ጨዋነትን የሚያጓድሉ  ነውጠኛ ተጫዋቾች ተለይተው እርምጃ እንዲወሰድም ጠይቀዋል፡፡

በመጠጥ ቤቶችና በአላስፈላጊ ቦታዎች የሚታዩ ተጫዋቾች መበራከትና ከሜዳ ውጭ በክለቡ ውስጥ የሚስተዋለዉ የሥነ ምግባር ችግር፣የክለቡን የአንድነት መንፈስ በማበላሽት በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ተሳትፎው አስተማማኝ እንዳይሆን ማድረጉም ተገልጿል።   

ከጨዋታ ደንብና ህግ ውጭ በስሜታዊነት ማሸነፍን ብቻ ዓላማ አድርጎ መደገፍ ለህገ-ወጥ ተግባራት መነሻ መሆን እንደማይገባውም ተሳታፊዎቹ በሰጡት አስተያየት ጠቁመዋል።

ከስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት ጋር ተያይዞ በሚከሰቱ ተግባራት የሕዝቡ ሰላም መናጋት እንደሌለበትም ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።

ክለቡ ኢትዮጵያን ወክሎ በአፍሪካ ኮንፈደሬሽን ዋንጫ ያሳየው ጠንካራ ተሳትፎና በቮሊ ቦል እያሳየ ያለው ውጤት ቀጣይነት እንዲኖራቸው መሥራት እንደሚገባ ተመልክቷል፡፡

በእግር ኳስ ከ17ና 20 ዓመት በታች የተቋቋሙት ቡድኖች በስፖርታዊ ጨዋነትና በውጤታማነት ረገድ ያስመዘገቡት ደረጃ የተሻለ መሆኑም ተመስክሮላቸዋል፡፡

ክለቡ በሰው ኃይል አደረጃጀት፣በፋይናንስ አስተዳደር ግልጽነትትና ወጪ ቆጣቢነት መሻሻል እንደታየበት ተመልክቷል፡፡

በሜዳ ውስጥ ተጋጣሚ ተጫዋችና ዳኛ ላይ አግባብነት የሌላቸው ተግባራት በመፈጸም ለቅጣትና ተመልካቾችን የሚያነሳሳ ተጫዋች እንዲሁም ከአቅም በታች የሚጫወቱትንም ለማረም እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል፡፡

ከሜዳ ውጭ አላስፈላጊ ቦታዎች የሚገኙ ተጫዋቾችን ለማረም በማደሪያ ክፍሎች አብሮ በመቆየት ክትትል የሚያደርግ በአዲስ መልክ የቴክኒክ  ቡድን መደራጀቱን የገለጹት አቶ አሰፋ፣ የክለቡን የአንድነት መንፈስ ለማጠናከር ከተጨዋቾችና ከአሰልጣኞች ጋር ከልምምድና ከጨዋታ መልስ ልዩ ግምገማና ምክክር እንደሚኖር ተናግረዋል፡፡

የክለቡ ቦርድ ፕሬዚዳንት አቶ ፍሬው ሞገስ በበኩላቸዉ በጠቅላላ ጉባኤው የተነሱት ሃሳቦች ትክክል መሆናቸውን ገልጸው፣ ስፖርቱን በተገቢዉ ሁኔታ ባለመምራቱ እየተከሰተ ያለውንን ችግር መፍታት ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይሆንም ብለዋል፡፡

በሜዳ ዉስጥም ሆነ ከሜዳ ዉጭ ስፖርቱ ይጠቅመኛል፤በስፖርቱ ጉዳይ ያገባኛል የሚል አካል ህዝብን ማክበር ይገባዋል ያሉት አቶ ፍሬው በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ህግንና ደንብ እንደሚተገበሩ ተናግረዋል፡፡

ስፖርታዊ ጨዋነትን በማስፈን ላይ ትኩረት የሚያደርግ የደጋፊ ማህበር እንደሚቋቋም  አቶ ፍሬው አስታውቀዋል፡፡

ጠቅላላ ጉባዔው የ2010 የሥራ ዓመት ክንዉን ሪፖርት፣የዓመቱ ሂሳብ በገለልተኛ ኦዲት ተጣርቶ እንዲሁም የ2011 ዕቅድን አጽድቋል፡፡

ጠቅላላ ጉባዔው ክለቡን የሚመሩ 11 አባላት ያሉት የሥራ አስፈጻሚ አባላት ምርጫ አካሂዷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም