ፖሊተር የተሰኘ አዲስ የአፈር ማዳበሪያ ስራ ላይ ሊውል ነው

67

ወልመራ ጥር 5/2011 የግብርና ሚኒስቴር ፖሊተር የተሰኘ አዲስ የአፈር ማዳበሪያ ማስተዋወቅ ጀመረ።

ማዳበሪያው ለሁሉም የአፈርና የምርት አይነት ተስማሚ መሆኑ ዛሬ በኦሮሚያ ክልል ወልመራ ወረዳ ለሙከራ ሲቀርብ ተገልጿል።

ፖሊተር በተሰኘ የፈረንሳይ ኩባንያ የተመረተው ማዳበሪያ በአንድ ሄክታር መሬት ላይ 10 ኪሎ ግራም መጠቀም ያስችላል ተብሏል።

አንድ ጊዜ ጥቅም ላይ ከዋለ ከሶስት እስከ አምስት ዓመት መሬቱ ያለ ተጨማሪ ማዳበሪያ ተመሳሳይ ምርት መስጠት እንደሚያስችልም እንዲሁ።

በግብርናና በኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴሮች ትብብር ወደ አገር ቤት የመጣው ማዳበሪያ ምርትና ምርታማነት ያሳድጋል፣ ለሁሉም የአፈር አይነት ተስማሚ በመሆኑም አሲዳማ መሬትን በኖራ ለማከም ይወጣ የነበረውን ወጪ ያስቀራል ተብሏል።

በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የግብርና ሚኒስትሩ አማካሪ ዶክተር ኢያሱ አብርሃ እንዳሉት ማዳበሪያው ጥቅም ላይ ሲውል ለአጠቃቀም ምቹና በመጠንም አነስተኛ በመሆኑ ለማዳበሪያ ግዥና ማጓጓዣ ይወጣ የነበረውን ወጪ ይቀንሳል፤ በውሃ አጠር መሬት ላይም መጠቀም ይቻላል።

የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው ግብርናን ለማዘመን በቴክኖሎጂ መደገፍ የሚያስችልና አገሪቱ የጀመረችውን ልማት የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

በዛሬው ዕለት በወልመራ የተሞከረው የፖሊተር ማዳበሪያ ውጤታማነት ታይቶ በቀጣዩ ዓመት በስፋት ወደ አገር ውስጥ እንደሚገባ ተገልጿል።

ፖሊተር የአፈር ማዳበሪያ በአውሮፓ፣ በደቡብ አሜሪካና አፍሪካ የተለያዩ አገሮች ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም